ፕሬዝዳንቷ ተመራቂ ፖሊሶች ዜጎችን ያለአድልኦ እንዲያገለግሉ አደራ ሰጡ።

43

ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከሰርትፍኬት እስከ ማስተርስ መርሐ-ግብር ያሰለጠናቸውን 623 ሰልጣኞች በዛሬው ዕለት በሰንዳፋ አስመርቋል።

በሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት እንዲሁም በአሥተዳደር ሥራ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ 41 ሰልጣኞችን በማስተርስ ለምርቃት በቅተዋል።

በተለያዩ ክልሎች ልዩ ኃይል የነበሩ 312 ሰልጣኞችም የምርቃቱ አካል መሆናቸው ተገልጿል።

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እና ሌሎች ተጋባዦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር መስፍን አበበ በዘመናዊ የፖሊስ ሥርዓት ውስጥ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረግ ተልዕኮውን እየተወጣ ዛሬ ላይ ደርሷል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የሀገራችንን የፖሊስ ሙያ ለማዘመን የተለያዩ የትምህርት ሥርዓቶችን ዘርግቶ በጥራት እና በጥናት እያስተማረ እንደሆነም ገልጸዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፣ የፌዴራል ፖሊስ በሪፎርም ሥራ ሕዝብን እና ሀገርን ያስቀደመ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት እየሠራ ነው ብለዋል።

የወንጀል ምርመራ ሥራዎችን ሙያዊ በሆነ መንገድ እንዲከውንም ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፣ ከሠራዊቱ አብራክ የወጣ አመራር መኖሩ ለኢትዮጵያ የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ዕድገት እና ለፖሊሳዊ ሙያ መሻሻል አስተዋፅኦው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሙስናን፣ ወንጀልን ፅንፈኝነትን የምትዋጉ፤ የዜጎችን መብት የምታስከብሩ፤ ዜጎችን ያለአድልኦ እንድታገለግሉ ሲሉም ፕሬዚዳንቷ ለተመራቂዎቹ አደራቸውን ሰጥተዋል።

በተያያዘም የኢትዮጵያ የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ማኅበረሰብ 30 ሚሊየን ብር በማውጣት ያስገነባው የአስፋልት መንገድ በፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ተመርቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ወሎ ዞን የጊምባ ከተማ አሥተዳደር ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን አስመረቀ ።
Next articleየደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አቶ መንበሩ ዘውዴ አስራትን የከተማዋ ከንቲባ አድርጎ ሾመ።