የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን በመቁረጥ ሲያጓጉዙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

117

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 07/2012ዓ.ም (አብመድ) የኤሌክትሪክ ሽቦዎችን ከቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችና ከወዳደቁ የፕላስቲክ ዕቃዎች ጋር በማደባለቅ ከገብረ ጉራቻ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት የሞከሩ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ግምቱ በውል ያልታወቀ የኤሌክትሪክ ሽቦን ከሱሉልታ ፍተሻ ኬላ ለማሳለፍ ሲሞክሩ ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በፌዴራል ፖሊስ የትራፊክ ፍሰት ተቆጣጣሪዎች እና ወንጀል መከላከል አባላት እጅ ከፍንጅ መያዙን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ፋብኮ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በወንጀል መከላከል ዘርፍ ፀጥታና ሕግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዋና ኢንስፔክተር አብዲሳ ዋቅጅራ ‹‹የኅብረተሰቡን ጥቆማ መሠረት በማድረግ ተጠርጣሪዎቹ ኬላው ላይ ይደርሳሉ በተባለበት ሰዓት የተጠናከረ ቁጥጥር በማድረግ የመንግሥት ንብረት የሆነውን የኤሌክትሪክ ሽቦ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል›› ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንገዶች ትራፊክ ቁጥጥርና አደጋ ምርመራ ቡድን መሪ ምክትል ኢንስፔክተር ዳዊት አሰፋ ደግሞ ‹‹በልማት አውታሮች ላይ የሚፈጸም ዝርፊያ ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች ምን ጊዜም ከሕግ አስከባሪውም ሆነ ከኅብረተሰቡ ሊደበቁ እንደማይችሉና የሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ይህ የተጠናከረ የቁጥጥር ተግባር ማሳያ ይሆናል›› ብለዋል፡፡

Previous articleአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን እያከበረ ነው፡፡
Next articleአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው፡፡