በኮሌጁ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሥራ ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ።

37

ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን የቡሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ2015 ዓ.ም ከደረጃ 3 እስከ ደረጃ 5 በ9 የሙያ ዘርፎች በመደበኛውና በማታው መርኃ ግብር ሲሰለጥኑ የቆዩ 325 ተማሪዎችን ለ20ኛ ጊዜ አስመርቋል።

በክልሉ ከሚገኙ 10 የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች መካከል አንዱ የሆነው ኮሌጁ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እንዲሁም ለኢንዱስትሪዎች በማፍራት ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ሲሉ የኮሌጁ ዲን አቶ አስጨነቅ ካሳ ተናግረዋል።

ቡሬ ከተማ የኢንዱስትሪ መንደር እየሆነች በመምጣቷ ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኮሌጁ አዳዲስ እና ምርጥ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት ወደ ኢንዱስትሪው በማስገባት አቅም ሆኗል።

ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በምርምር በማቅረብ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ችግር እየቀረፈ መሆኑንም አቶ አስጨነቅ ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የቡሬ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አበጀ ሙላት ለተመራቂ ተማሪዎችና ወላጆች የእንኳን ደስአላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታችሁ በንድፈ ሃሳብ ያገኛችሁትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ መሰማራት አለባችሁ ብለዋል።

ከንቲባው የዛሬ ተመራቂዎች ባገኛችሁት እውቀት ሙያዊ ዲስፕሊንን ተላብሳችሁ ሀገራችሁንና ሕዝባችሁን እንድታገለግሉ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ተመራቂ ተማሪዎችም በኮሌጁ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የቡሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ባለፋት 20 ዓመታት ከ30 ሺህ 325 ሰልጣኞችን የሙያ ባለቤት በማድረግ ወደ ሥራ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ከኮሌጁ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ:- ዘመኑ ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እስካሁን ድረስ ዝናብ ያላገኙ ቀበሌዎች አሉ” የምሥራቅ በለሳ ወረዳ
Next articleበደቡብ ወሎ ዞን የጊምባ ከተማ አሥተዳደር ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን አስመረቀ ።