“እስካሁን ድረስ ዝናብ ያላገኙ ቀበሌዎች አሉ” የምሥራቅ በለሳ ወረዳ

29

ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዝናብ እጥረት በእንስሳት እና በሰው ሕይዎት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት ማሳደሩን የምሥራቅ በለሳ ወረዳ አስታውቋል፡፡

ወረኃ ሐምሌ ነው፡፡ በኢትዮጰያ ሰማይ ሥር ዝናብ የሚመበዛበት፡፡ ሰማይ ጉም አዝሎ ዝናብ የሚያፈስስበት፣ ተራራዎች በጉም ተሸፍነው የሚውሉበት፣ አፍላጋት ሞልተው የሚደነፉበት፣ የደረቀው መሬት የሚለመልምበት፣ ሜዳውና ሸንተተረሩ ሁሉ አረንጓዴ ካባ የሚለብስበት፣ ላሞች ከለመለመው መስክ ውለው ወተት የሚሰጡበት፣ በሬዎች ከለመለመው መስክ ግጦሽ እየጋጡ አጎልብተው የሚያርሱበት፣ ፍየልና በጎች ሁሉም ለምለም ግጠው ጠግበው የሚመለሱበት ነው፡፡

በበለሳ ግን በወረኃ ሐምሌ አፍላጋት እንደደረቁ ነው፡፡ ሰማዩ ዝናብ አላወረደም፣ ምድሩ በአረንጓዴ ካባ አልተሸፈነም፣ ላምና በሬዎች፣ ፍየልና በጎች ተርበዋል፣ ለምለም እሳር ናፍቀዋል፣ ለወትሮው ሰማይና ምድሩ ውኃ በሚበዛበት በወረኃ ሐምሌ የሚጠጡት ውኃ ተቸግረዋል፣ የሚመገቡት ለምለም እሳር አጥተው ለረሃብ ተጋልጠዋል፡፡ በዚያች ምድር ክረምት የሚቀር መስሏል፡፡ ለምን ካሉ በወረኃ ሐምሌ ዝናብ አልታየምና፡፡ በተለይም የእንስሳት ሞት ቀርቧል፣ ጎናቸው በረኃብ ተወግቷል፣ ጉሮሯቸው በውኃ ጥም ደርቋልና፡፡

የምሥራቅ በለሳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሻ ቡድን መሪ ሽፈራው ማሞ በወረዳው አሁን ድረስ የዝናብ ጠብታ ያለገኙ ቀበሌዎች መኖራቸውን ነግረውኛል፡፡ በወረዳው ካሉ 30 ቀበሌዎች መካከል በ18ቱ ቀበሌዎች እስከ ወረኃ ሐምሌ መጀመሪያ ቀናት ድረስ ዝናብ አልነበረም፣ ከሁለት ቀን ወዲህ አንዳንዶቹ መጠነኛ ዝናብ አግኝተዋል፣ አሁንም ግን ዝናብ ያልዘነበባቸው ቀበሌዎች አሉ ነው ያሉት፡፡

ባለፈው ዓመትም በድርቅ ተጎድቶ የነበረው አካባቢ በዚህ ክረምት ይካሳል ተብሎ ሲጠበቅ ዘንድሮም ደግሞታል፡፡ አሁን ለሰዎች የምግብ እጥረት፣ ለከብቶች የመኖና የውኃ እጥረት አለ፡፡ ለወትሮው የውኃ ችግር ያለበት አካባቢ ይባስ ብሎ በሐምሌም ምድሩ ሲደርቅ የውኃ ችግሩ አይሏል፡፡

በእንስሳት ላይ የምግብ እና የውኃ እጥረት በመኖሩ እንስሳት ላይ በሽታ ሊከሰት እንደሚችልና ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋት ተፍጠሯል ነው ያሉት፡፡ በእንስሳት ላይ ብቻ ሳይሆን በሰዎች ላይም በሽታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ስጋት አለ ብለዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች በረሃብ ያልተጎዱትን ሸጠው ቀን እስኪያልፍ ብራቸውን በባንክ እንዲያስቀምጡ፣ ካለበለዚያም ዝናብ ወዳለበት አካባቢ እየወሰዱ እንዲያከርሙና ክትባት እንዲያስከትቡ የማግባባት ሥራ እየሠሩ መሆናቸውንም ነግረውኛል፡፡

ባለፈው ዓመትም ድርቅ እንደነበር ያስታወሱት ቡድን መሪው እናቶች፣ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ አቅም ያላቸው ደግሞ ጊዜው እስኪያልፍ የቀን ሥራዎችን ቢሆን እየሠሩ ራሳቸውን ቤተሰቦቻቸውንም እንዲደግፉ የማግባበት ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት በነበረው ድርቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተለይተው ቢጠየቅም ድጋፍ የተደረገው ለተወሰኑ ወገኖች ብቻ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ቀሪው ሕዝብ የምግብ ድጋፍ ሳያገኝ መኖሩን የተናገሩት የቡድን መሪው ድጋፍ የተደረገላቸውም ለአንድ ወር ብቻ እንደተሰጣቸው ማቆሙን ነው የገለጹት፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ የምግብ እጥረት መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ ለሰዎችም ሆነ ለእንስሳት አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የምሥራቅ በለሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ታምራት አስረሳኸኝ በወረዳቸው አንድም ቀን ዝናብ ያልጣለባቸው ቀበሌዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በወረዳው ያለው የዝናብ መጠን ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡ በአጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት እንስሳት እየተጎዱ ነው ብለዋል፡፡ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ አስቀድሞ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል፡፡

ወረዳው ዝናብ አጠር መሆኑን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የደን ሃብትን በማስፋፋትና የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ላይ በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ደኖች እንዳይመነጠሩ በመከላከል የተፈጥሮን ሚዛን ለመጠበቅ እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተደጋጋሚ በድርቅ የተጎዳውን አካባቢ ለመታደግ አፋጣኝ ድጋፍ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሐፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ መብራቱ ደጉ በዞኑ ምሥራቅ በለሳ እና ኪንፋዝ በገላ ወረዳዎች ላይ የዝናብ እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡ በምዕራብ በለሳም ቆላማ አካባቢዎች ችግሩ እንዳለ ነው ያመላከቱት፡፡
ያም ሆኖ በምዕራብ በለሳ የዝናብ እጥረት ችግር አለ ማለት የሚያስችል ደረጃ ላይ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ሌሎች ወረዳዎች ጥሩ የሚባል የዝናብ ስርጭት መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡

በዞኑ የተከዜ ተፋሰስ የሆኑ ወረዳች የዝናብ እጥረት የሚያጋጥማቸው መሆናቸውን ነው የገለፁት፡፡

ምሥራቅ በለሳ ወረዳ በየጊዜው ለድርቅ የሚጠቃ ወረዳ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የዝናብ እጥረት በሚከሰትባቸው ወረዳዎች አስቀድሞ ጥናት በመስራት ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳውቁ የተናገሩት ቡድን መሪው የገጠመውን ችግር የሚያጠና ቡድን ወደ ሥፍራው እንደሚያቀናና የችግሩን መጠን በማረጋገጥ ድጋፍ የሚደረግበትን መንገድ እንደሚያመቻች ነው የገለፁት፡፡

ችግሩን በማረጋገጥ ምላሽ የሚገኝበት መንገድ ይመቻቻልም ነው ያሉት፡፡ የክልሉን መንግሥት አስቀድመው ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡ የከፋ ችግር እንዳይገጥም የቴክኒክ ኮሚቴው በፍጥነት አይቶ እንደተመለሰ ወደ ሚመለከተው አካል ግፊት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመውጫ ፈተናውን ከወሰዱት 40 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች ፈተናውን አልፈዋል” የትምህርት ሚኒስቴር
Next articleበኮሌጁ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሥራ ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ።