አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው፡፡

154

አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ጌትነት ይርሳው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በዘርፉ ውድድር በበዛበት በዚህ ሉላዊ ዘመን በሚያስገርም ፍጥነት እያደገ የመጣው የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በክልላችን ብሎም በሀገሪቱ በዘርፉ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት አሁን ያለበት ደረጃ የሚያኮራ መሆኑንና በርካታ ፈተናዎች፣ ጥያቄዎች እና ጫፍ ረገጥ ፍላጎቶች በሚታዩበት በዚህ ዘመን የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እያሰፈረ እንደሚገኝ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንደ አብመድ ዓይነት ትላልቅ የሚዲያ ተቋማት የሰፊውን የአማራ ሕዝብ ፍላጎት መሠረት በማድረግ አስተውሎ ወደ ፊት መራመድ እንደሚገባቸውም አቶ ጌትነት አሳስበዋል፡፡

በቀጣይ የድርጅቱ ጉዞም የ25 ዓመታት መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር፣ የጎደለውን በማረም፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በዕውቀት ራሱን ከዘመኑ ጋር አዘምኖ በሚሠራባቸው ወርቃማ ሥራዎች ለወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉ ለመድረስ ይችል ዘንድ ተግቶ እንዲሠራ አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥትም ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርግ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ከዚህ መድረስ አስተዋጽኦ ለነበራቸው የድርጅቱ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች፣ ለክልሉ መንግሥት፣ በገንዘብም ሆነ በሐሳብ እገዛ ሲያደርጉ ለነበሩ አካላት ሁሉ አቶ ጌትነት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው

Previous articleየኤሌክትሪክ ሽቦዎችን በመቁረጥ ሲያጓጉዙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
Next articleየአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎች በክልሉ ኢንቨስትመንት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ሲያትል ገቡ፡፡