“የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ትልቁ አቅማችን ትብብራችን ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

26

ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ሕዝባዊ የንቅናቄ መድረክ በባሕርዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ውስጥ ለትክክለኛ መማር ማስተማር የሚመጥን ደረጃ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ከ17 በመቶ እንደማይበልጡ ተናግረዋል። አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መኾናቸውን በመገንዘብ ሕዝቡ፣ ባለሃብቶች እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም መረባረብ እንዳለባቸውም አንስተዋል።

ትምህርት ቤቶች ሕጻናትን የሚስቡ እና ከአካባቢ ንጽህና እና ውበት ጋር የተላመዱ ኾነው እንዲገነቡ ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። “የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ትልቁ አቅማችን ትብብራችን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ዶክተር ይልቃል በመምህራን ሥልጠና ላይ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው መምህራንን በአግባቡ አሰልጥኖ እና ተገቢውን ክብር በመስጠት ወደ ሥራ በማሰማራት ትውልድ የመቅረጽ ተግባርን ማሳለጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሕዝብ የሰጠውን ኃላፊነት ሳያዛንፍ የሚወጣ ትውልድ ለመፍጠር የመምህራን ሚና ጉልህ ስለመኾኑም ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። የአማራ ክልል መንግሥት ካለው ሰፊ የመልማት ፍላጎት አንጻር ለትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻል እና ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ስለመኾኑም ዶክተር ይልቃል አመላክተዋል። “የምናልመው እድገት ላይ ለመድረስ ትውልዱን በዕውቀት ማነጽ ግድ ይላል” ሲሉም ተናግረዋል።

በክልሉ በርካታ ባለሃብቶች በግል ተነሳሽነት ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ገንብተው ለትውልድ ማበርከታቸውን አንስተው ሌሎች ባለሃብቶችም እንዲህ አይነት የማይዘነጋ በጎ ተግባር እንዲፈፅሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገር እና ሕዝቡን የሚወድ ሁሉ ለትውልድ ምንጭ የኾኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ይነሳ” ማተብ ታፈረ (ዶ.ር)
Next article“የመውጫ ፈተናውን ከወሰዱት 40 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች ፈተናውን አልፈዋል” የትምህርት ሚኒስቴር