
ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከ43ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጎን ለጎን ከአፍሪካ ሀገራት ልዑካን ጋር ስኬታማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረግ መቻሉን ምክትል ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ለሁለት ቀናት በኬንያ ናይሮቢ ሲካሄድ የቆየው የምክር ቤቱ ስብስባ ተጠናቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደገለጹት ከመደበኛው ስብስባ ጎን ለጎን ከ10 አገራት በላይ ልዑካን ጋር የሁለትዮሽ እና የጎንዮሽ ውይይት ተደርጓል።
በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እንዲሁም ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ትብብር የምትፈልጋቸውን አጀንዳ በመለየትም ውጤታማ እና ስኬታማ ውይይት ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በውይይቶቹ በተነሱ ሀሳቦች ላይ በቀጣይ የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
ከጉባኤው አጀንዳዎች አንዱ የሆነውና የ2024 የኮሚሽኑን በጀት የተመለከተው ጉዳይ አሁን ያለውን የኑሮ ሁኔታና ኮሚሽኑንም ሊያሰራ በሚችል መልኩ እንዲከናወን የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።
በስብስባው በአፍሪካ ኅብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የስራ አፈጻጸም ላይ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ ዋና መቀመጫውን ያደረገው የአፍሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል(አፍሪካ ሲዲሲ) ወደ ተሟላ አገልግሎት እንዲገባ ኢትዮጵያ አቋሟን እና ምክረ ሀሳቧን አጋርታለች ነው ያሉት አቶ ደመቀ።
የሁለተኛ ዙር የማዕከሉ ግንባታ በተፋጠነ መልኩ ወደ ግንባታ እንዲገባም ኢትዮጵያ ጥሪ ማቅረቧን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የተለያዩ ማሻሻያዎች እያደረገ እንደሚገኝ እና የማሻሻያው አንድ አካል የሆነው በአዲስ ጥናት እና መዋቅር ለተቋሙ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል መወሰንና ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ማሻሻያው የተቋሙን ፍላጎት እና የሰራተኞቹን መብት ያጣጠመ እንዲሆን በተለይም በሕብረቱ ካሉ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች አኳያ ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ ትግበራ እንዲኖር ኢትዮጵያ ጥሪ ማቅረቧንና ጉዳዩን በቅርበት እንደምትከታተለው መግለጿንም ነው አቶ ደመቀ ያብራሩት።
በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችም ላይ ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!