
አዲስ አበባ: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመገናኛ ብዙሃን መሪዎች ፣ባለሙያዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች በአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ የእጽዋት ማዕከል በዛሬው እለት ችግኝ ተክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ እንደገለጹት በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከ17 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዷል። በጉለሌ እጽዋት ማዕከል በዛሬው ዕለት ከ10 ሺህ በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ኀላፊዋ ገልጸዋል።
ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 20 በመቶ የፍራፍሬ፣ 20 በመቶ የውበት ሲኾኑ 60 በመቶ ደግሞ የጥላ ዛፎች መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የአዲስ አበበ ከተማ አሥተዳደር ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኀላፊ አቶ ጀማሉ ጀምበር ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ለጽድቀት መጠናቸው መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አቶ ጀማሉ ለዘንድሮው የችግኝ ተከላ ስኬት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣና ችግኞችን እንዲተክል ጥሪ አቅርበዋል።
ታዋቂ ግለሰቦች እና የመገናኛ ብዙሃን መሪዎች የችግኝ ተከላው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ :-ዳንኤል መላኩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!