“የእርሻ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መሬታችንን በዘር ለመሸፈን በትጋት እየሠራን ነው” በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚገኙ አልሚ ባለሀብቶች

51

ሁመራ: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ያገኘውን ነጻነት አስጠብቆ በመዝለቅ ተፈጥሮ በሰጠችው መልክዓ ምድር ለምግብ ፍጆታ ፣ ለኢንዳስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገቢያ የሚያገለግሉ ሰብሎችን እያለማ ይገኛል። የአካባቢያቸውን ሰላም አስጠብቀው መዝለቅ የቻሉት የዞኑ ነዋሪዎች በ2015/16 የምርት ዘመን መሬታቸውን ቀድመው በማለስለስና ለእርሻ ዝግጁ በማድረግ መሬታቸውን በዘር እየሸፈኑ ነው።

በቃብትያ ሁመራ ወረዳ መሬታቸውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በዘር በመሸፈን ላይ ያገኘናቸው አልሚ ባለሃብት አቶ ሹምየ ዓለምነህ በባለፈው ዓመት የምርት የምርት ዘመን ውጤታማ መኾናቸውን ተናግረዋል። በዘንድሮው የምርት ዘመንም 1 መቶ ሄክታር መሬታቸውን በሰሊጥና ማሽላ ለመሸፈን እየሠሩ መኾኑን ነው የተናገሩት። ከዘር ወቅት ጀምሮ እስከ ምርት መሰብሰቢያ ድረስ የጉልበት ሠራተኛ የሚያስፈልግ በመኾኑ ወደ ዞኑ የተለያዩ ሠራተኞች እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል ።

ሌላኛው መሬታቸውን በዘር በመሽፈን ላይ ያገኘናቸው የአይቸው አላየሁ የእርሻ የግል ድርጅት ተወካይ ሙሉየ ጌታ መሬታቸውን ቀድሞ በማለስለስ ከ10 ብሎክ በላይ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈናቸውን አንስተዋል። በምርታቸው ውጤታማ ለመኾን በቁርጠኝነት ትጋት እንደሚያደርጉ ያነሱት አልሚ ባለሃብቶቹ መንግሥት የነዳጅና የኬሚካል አቅርቦትን እንዲያሟላላቸው ጠይቀዋል። የእርሻ ሥራቸውን በወቅቱ ለማከናወን የነዳጅ እጥረት ፈተና እንደሆነባቸውም አንስተዋል። የባለሙያ ድጋፍ አነስተኛ መኾኑን የተናገሩት ባለ ሃብቶቹ በቅርበት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጠይቀዋል።

በዞኑ በ2015/16 የምርት ዘመን ከ5 መቶ 61 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሠራ መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ብድን መሪ አቶ ኑርሴን አብዱልቃድር ገልጸዋል። የባለሙያ እጥረት በመኖሩ በሚፈለገው ልክ ድጋፍ ማድረግ እንዳልተቻለ ያነሱት አቶ ኑርሴን ባሉ ባለሙያዎች በቁርጠኝነት ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በዞኑ እየለማ ከሚገኘው መሬት ውስጥ 40 ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በሰሊጥና ማሽላ ምርት እንደሚለማም አንስተዋል። በዞኑ እያጋጠመ ያለውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ከዞኑ ንግድ ገቢያ ልማት መምሪያ ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ያሉት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ አወቀ መብራቱ ናቸው።

የጸረ አረምና የጸረ ተባይ ኬሚካሎችን ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው ዳንሻ ከተማ ላይ ዩኒየን በመክፈት ለባለሃብቶችና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ተሠርቷል ብለዋል። በሁመራ ከተማ የኬሚካል አቅርቦት ማሰራጫ ዩኑየን ለመክፈት በሂደት ላይ መኾኑን አንስተዋል።

ዘጋቢ ያየህ ፈንቴ

Previous articleተጀምረው በተለያየ ምክንያት የተቋረጡ የጤና ተቋማት ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።
Next articleየመገናኛ ብዙሃን መሪዎች ፣ባለሙያዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች በጉለሌ የእጽዋት ማዕከል የችግኝ ተካላ አካሄዱ።