
ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው ግንባታው ተቋርጦ የነበረውን የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕጻናትና እናቶች ማቆያ ክፍል ግንባታ ለመጨረስ ውል ሰጥቷል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተጀምረው በተቋራጮች አቅም ውስንነት እና በሌሎችም ምክንያቶች የተቋረጡ የጤና ተቋማት ይገኛሉ። የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ ተጀምረው የተቋረጡ ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች የክልሉን የጤና ሽፋን ተደራሽነት እንደሚጎዱ ተናግረዋል። ግንባታዎችን በፍጥነት እና በጥራት በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ለማስገባት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕጻናትና እናቶች መቆያ ሕንፃ ግንባታ በአዲስ መልኩ ለተቋራጭ ከተሰጡ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው። ግንባታው የተጀመረው በ2006 ዓ.ም እንደነበር ምክትል ቢሮ ኀላፊው አንስተዋል። ሕንጻው ለ10 ዓመታት የተጓተተ ሲኾን የቀድሞው ተቋራጭ ውል ተሰርዞ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የአማራ ሕንጻ ሥራዎች ግንባታ ድርጅት አዲስ ውል ወስዷል። የሕንጻ ሥራው በሁለት ዓመታት ውስጥ በጥራት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አቶ አብዱልከሪም ተናግረዋል።
ሥራውን ለማጠናቀቅ በተቋራጭነት የወሰደው የአማራ ሕንጻ ሥራዎች ግንባታ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታደሰ ግርማ ድርጅቱ በጤና ተቋማት ግንባታ አፈጻጸም ሰፊ ልምድ ያለው ስለመኾኑ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት 22 የክልሉ ጤና ተቋማትን በተቋራጭነት ወስዶ 21 የሚኾኑትን በጥራት እና በፍጥነት ገንብቶ ስለማስረከቡም አንስተዋል። ይህን መልካም ተሞክሮ በመጠቀም ሥራው ቁሞ የነበረውን የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም በጥራት እና በፍጥነት አጠናቅቀን ለባለቤቱ እናስረክባለን ነው ያሉት። ብቁ ባለሙያዎችን እና የግንባታ መሣሪያዎችን የመመደብ ሥራ ከወዲሁ እየተከናወነ ስለመኾኑም አቶ ታደሰ ተናግረዋል።
የአማካሪነት ቀሪ ሥራዎችን ለመፈጸም ውል የወሰደው ደግሞ ልኅቀት የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ነው። የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ውቤ አጥናፍ በበኩላቸው ግንባታው በጥራት እና በፍጥነት እንዲሠራ አስፈላጊውን ሁሉ ክትትል እና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። ግንባታው ለክልሉ መንግሥት የልማት ድርጅት በተቋራጭነት መሰጠቱ በፍጥነት ተጠናቅቆ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲበቃ ያስችላል ሲሉም አቶ ውቤ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!