
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 07/2012ዓ.ም (አብመድ) በበኩር ጋዜጣ ሕትመት የጀመረው አብመድ የሚዲያ ጉዞ ዛሬ ላይ በሕትመት፣ በኤሌክትሮኒክስ እና በዲጂታል ሚዲያው ተወዳዳሪ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ከክልል ሚዲያዎች ቀዳሚ የሆነው የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዛሬ 25ኛ ዓመት ምሥረታ በዓሉን እያከበረ ነው፡፡
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሙሉቀን ሰጥዬ በሥነ ሥርዓቱ መክፈቻ ላይ ድርጅቱ ከዚህ እስኪደርስ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ፣ አሁን በሥራ ላይ ላሉ፣ ከተቋ ለቅቀው በተለያየ ቦታ ለሚገኙና በሕይወት የሌሉ ለተቋሙ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ድርጅቱ በርካታ የሰው ኃይልና በቂና ዘመኑን የዋጁ የሚዲያ ቴክኖሎጂዎች መታጠቁን የገለጹት አቶ ሙሉቀን ‹‹ሲመሠረት ከነበረመት ሁኔታ በእጅጉ ያደገ የተመነደገ ሚዲያ ነው›› ብለዋል፡፡ በዓሉን የድርጅቱን ገጽታ ይበልጥ ለማስተዋወቅ፣ ለዚህ ያደረሱትን አካላት ዕውቅና ለመስጠትና በቀጣይ የበለጠ የሥራ መነሳሳት በመፍጠር ለላቀ ለውጥ ለመትጋት እንደመነሻ ለማድረግ ለመጠቀም መታሰቡንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው