
ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣቶች ከሀገራቸው ታሪክና ባሕል ጋር እንዲተዋወቁ የኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች እና የሃይማኖት ተቋማት ማገዝ ይገባቸዋል ተብሏል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተውጣጣ የልዑካን ቡድን በቀጠር ዶሃ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤትንና በግንባታ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ጎብኝቷል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት በቅድሚያ በዶሃ የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ጉብኝት አካሂደዋል። በወቅቱም ከትምህርት ቤቱ አመራሮች ጋር በተደረገው ውይይት ዳያስፖራው ልጆቹን የሚያስተምርበት ሁኔታ በመመቻቸቱ ታዳጊዎች የሀገራቸውን ታሪክና ባሕል አውቀው እንዲያድጉ ከማድረግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑ ተገልጿል። ይህ በጎ ጅምር እንዲጎለብት በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠይቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንንም የጎበኘ ሲሆን፣ በሃይማኖት አባቶች ሂደቱን በተመለከተ ለቡድኑ ገለጻ ተደርጎለታል። በወቅቱም የሃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት መንግሥት ቤተክሪስቲያኗ የቤተክርስቲያን መስሪያ ቦታ እንድታገኝ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽዖ፤ ኤምባሲውና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል። በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ትስስር እንዲጎለብት ለመሰል ተቋማት የሚሰጠው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
የቡድኑ አባላትም የቤተክርስቲያን ግንባታው የደረሰበት ደረጃ በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የዳያስፖራ አባላትና የሃይማኖት አባቶችን ኅብረት የሚያሳይ ነው ብለዋል። ግንባታው በጋራ እስከተሠራ ድረስ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ሊኾን የሚችል ተግባር መኾኑን ገልጸዋል፡፡ መረጃው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!