የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት የሥራ ኃላፊዎች የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ ሰጠ።

745

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 07/2012ዓ.ም (አብመድ) ማረሚያ ቤቶች የተወሳሰበ ባሕሪ ያላቸውን ታራሚዎችን የሚያስተናግዱ በመሆናቸው የፖሊስ አባላት ሠላም እና ዴሞክራሲያዊ መብት ማስከበር እና ማክበር ግዴታቸውን እንዲወጡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ አያሌው አሳስበዋል።

መብታቸውን ተረድተው የሚኖሩ ታራሚዎች እንደሚኖሩ ሁሉ ግዴታቸውን ባለመረዳት ተጨማሪ ጥፋት ለመፈጸም የሚያስቡም ስለሚኖሩ የፖሊስ አባላት ከሁሉም ነገር ነፃ እና ገለልተኛ በመሆን ማገልገል እንደሚገባቸው ነው አቶ ላቀ የገለጹት።

ማረሚያ ቤቶች እንደስማቸው የማስተማሪያ እና የማስተካከያ ተቋም መሆን እንደሚገባቸውም ተገልጧል። ‹‹ወንጀል ልምምድ ነው፤ ዛሬ ዶሮ የሠረቀ በአግባቡ ካልታረመ ነገ ዶሮ ላይ አያቆምም። ዛሬ ሰዎችን የፈነከተ ነገ የሰው ሕይወት ማጥፋቱ አይቀርም። በመሆኑም ታራሚዎች በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲወጡ አስተዋይ መምህር መሆን አለባችሁ። እናንተ ጥሩ አስተማሪ ሆናችሁ ታራሚዎች ወደ ኅብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ለምሬት እና ለበቀል የሚነሳሱ ሳይሆን ጥሩ ትምህርት ቤት መሆኑን እንዲመሰክሩ ማድረግ ይገባል›› ነው ያሉት አቶ ላቀ በመልዕክታቸው።

ከማንም የፖለቲካ እና ቡድናዊ አስተሳሰብ ጫና በመውጣት ለሙያና ሥነ ምግባር ተገዥ በመሆን ተቋሙን እንደስሙ ስነ ምግባር የሚያንጽ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። አቶ ላቀ ‹‹ፖሊስ የሕዝብ ደጀንነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ተቋሙን ማዘመን እና አሠራሩን ማሻሻል ተቀዳሚ ተግባር መሆን ይገባዋል፤ ክልሉም ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል›› ብለዋል።

የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ወንድማገኝ ወዳጅ እንደገለጹት በክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የፖሊስ መተዳደሪያ ደንብ የነበሩትን ጎታች አሰራሮች እና የመዋቅር ይሻሻል ጥያቄ የክልሉ ምክር ቤት ተቀብሎ ምላሽ በመስጠቱ ተቋሙ ሥራውን በሚፈልገው ጥራት ለማከናወን አንዲችል አድርጎታል። የተሰጠው የማዕረግ ዕድገትም የለውጡ ውጤት እንደሆነ ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።

የአሰራሮች መሻሻልም የአባላቱን የሥራ ተነሳሽነት ከማሳደግ ባሻገር ታራሚዎችንም በሙያ እና ሥነ ምግባር ታንጸው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት የሥራ ኃላፊዎች የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ ትናንት ማምሻውን ሰጥቷል። የሥራ ኃላፊዎቹ በማረሚያ ቤት ፖሊስነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ናቸው። ማረሚያ ቤት ኮሚሽኑ ለምክትል ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ እና ለኮማንደር አማረ ወርቁ ነው የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ የተሰጠው። የማዕረግ ዕድገቱን ያገኙት በአማራ ክልል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን መተዳደሪያ ደንብ የተቀመጡ መመዘኛዎችን አሟልተው በመገኘታቸው እንደሆነም ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ

Previous articleየአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በምሁራን አንደበት፡፡
Next articleአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን እያከበረ ነው፡፡