
አዲስ አበባ: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፈጠራ እድገትን ለማሳደግ እቅድ ተኮር አጋርነትን ለማመቻቸት እና በአፍሪካ የኢንሹራንስ ቴክኖሎጂ ዘርፉን ለመደገፍ ያለመ መድረክ በአዲስ አበባ በኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ፣ ኤፍ .ኤፍ.ዲ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትብብር አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።
ኤፍ.ኤስ.ዲ. ኢትዮጵያ:-
✍️የገበያው ባለድርሻ አካላት የፋይናንስ መዋቅር ተግዳሮቶችን መቅረፍ እንዲችሉ የሚያግዝ
✍️የፋይናንስ ገበያን በማሳለጥ ላይ የተሠማራ
✍️የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የልማት እቅድ የሚደግፍ
✍️አካታች እና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ አወቃቀር እንዲኖር የሚሠራ ተቋም ነው።
ተቋሙ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ከሚገኙ እንደ መንግሥት፣ የግል ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት እንዲኹም ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመኾን የፋይናንስ አካታችነት፣ የካፒታል ተደራሽነት እና የአየር ንብረት ፋይናንስ ተግባራት ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥነ ምሕዳር ውስጥ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ በቂ የግንዛቤ እና የውይይት መድረክ አለመኖር እንደኾነም በመድረኩ ተገልጿል።
የኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኤርሚያስ እሸቱ በመድረኩ እንዳሉት ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን የኢንሹራንስ ዘርፍ ለማሳየት እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ “ውይይቱ ለሰፊው የአፍሪካ ኢንሹራንስ እድገት የበኩላችንን እንድናደርግ ዕድል ይፈጥራልም” ነው ያሉት። ፈጠራን በማበረታታትና በማሻሻል አሠራሮችን ለማዘመን እንደሚጠቅምም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዳዲስ አሠራሮችን በመከተል ፈጠራን በማበረታታት፣ እወቀትን በመጋራት፣ ዘላቂ ዕድገትን ለማምጣት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ ፈጠራን በማበረታታት፣ እወቀት በመጋራት እና አዳዲስ አሠራሮችን በመከተል ዘላቂ ዕድገትን የሚያመጡ እና ለሁሉም ኢትዮጵያዊን የዋስትና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!