
ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል መደበኛ ባልኾኑ ሥራዎች የተሰማሩ ዜጎች የማኅበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ከኾኑ 12 ዓመታት ተቆጥሯል።
የመንግሥት ሠራተኞችን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግም ፍኖተ ካርታ ከተዘጋጀ ዓመታትን አስቆጥሯል።
ፍኖተ ካርታው በመላ ሀገሪቱ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችን የደመወዝ ክፍያና የኑሮ ሁኔታን ግምት ውስጥ ያስገባ ጥናትን መሠረት ያደረገ መኾኑን ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት መግለጹ ይታወሳል።
መደበኛ በኾኑ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች አገልግሎቱን በቀላሉ እንዲያገኙ ታስቦ የተዘጋጀው የማኅበራዊ ጤና መድኅን አገልግሎት በዓዋጅና በደንብ ቢጸድቅም በሥራ ላይ እየዋለ አይደለም።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሃብት አሰባሰብ፣ አሥተዳደር እና አጋርነት ዳይሬክተር አዲሱ አበባው ቢሮው የማኅበረሰቡን የጤና መድኅን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ የመንግሥት ሠራተኛውን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ ያከናወነውን ሥራ አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት የመንግሥት ሠራተኛው ከደመወዙ በወር ሦስት በመቶ፣ ሦስት በመቶ ደግሞ በመንግሥት ተሸፍኖ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲኾን የሚያስችል ዓዋጅ እና ደንብ ወጥቷል።
አገልግሎቱን ለማስጀመርም በክልሉ የሚገኘው የመንግሥት ሠራተኛና የቤተሠብ ብዛት እንዲሁም የደመወዝ መጠን መረጃ ተሠብስቧል፤ ከመንግሥት ሠራተኛው የሚሰበሰበውና በመንግሥት የሚሸፈነው በጀት መጠንም ተሠርቶ ቀርቧል፤ አገልግሎቱን ለመሥጠት የሚያስፈልገው መታወቂያም ተዘጋጅቷል፤ ጤና ተቋማትም አገልግሎቱን መስጠት እንዲችሉ በባለሙያ የማደራጀት እና ግብዓት የማሟላት ሥራ ተሠርቷል። አገልግሎቱን ከመንግሥት ተቋማት ባለፈ በግል የጤና ተቋማት ለመስጠት የሚያስችል ዓዋጅና ደንብም ወጥቷል ብለዋል።
ከፌዴራል መንግሥት በጀት እንደተለቀቀ አገልግሎቱን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!