“መምህራን የሀገር ግንባታ እና የትውልድ ብርሃን መሰረቶች ናቸው” ማተብ ታፈረ (ዶ.ር)

72

ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ዓመታዊ የመምህራንን ቀን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው። በመድረኩ በሀገር ግንባታና የትውልድ ልዕልናን በማንበር ረገድ የመምህራን ሚና ተወስቷል። መምህራን በትውልድ ቀረጻና በሀገር ግንባታ ለውድቀቱም ኾነ ለስኬቱ የስልጣኔና ዝማኔ መሰረቶች ስለመኾናቸው በስፋት የተወሳ ጉዳይ ነው።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ትምህት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) “መምህራን የሀገር ግንባታ እና የትውልድ ብርሃን መሰረቶች ናቸው” ብለዋል። እንደ ሀገር ለሚታየው ስኬትም ይሁን ውደቅት ቀዳሚው የትምህርት ዘርፉ አሻራ ቀድሞ እንደሚጠቀስ ነው ያስረዱት።

አስቀድሞም የሀገር መሪውን፣ ፖለቲከኛውን፣ ሠራተኛውን፣ እራሱን መምህሩንም የፈጠሩት ትምህርትና መምህራን ናቸው ያሉት ቢሮ ኀላፊው ለውድቀቱም ለስኬቱም ባለቤቶች መምህራን ስለመኾናቸው ነው በአጽንዖት የተናገሩት። እንደ ዶክተር ማተብ ማብራሪያ መምህራን የትምህርት ሥርዓቱ ማሳያም ናቸው። ጠንካራ የትምህርት ሥርዓትን ማንበር የሚቻለው በጠንካራና በትውልድ ቀራጭነት ሚናቸው በላቁ መምህራን ነው፤ ትውልድ ከልኩ ቢዛነፍ፣ የፖለቲካ ሥርዓቱ ስብራት ቢገጥመው፣ የትምህርት ሥርዓቱ ቢወድቅ መነሻ ምክንያቱ መምህራን ይኾናሉ ነው ያሉት። አስቀድሞ በቀረጻቸው ዜጎች የመጣ ስብራት የሚታከመውም በመምህራን እንደኾነም በማሳሰብ። የትውልዱን ተስፋ ለመትለም የመምህራን አደራና ኀላፊነት ከምንም ቅድመ ሁኔታ በላይ ነው ብለዋል ዶክተር ማተብ።

ምናልባትም መምህራን በሥራቸውና በኑሯቸው የአሥተዳደራዊ አለመመቸት ሊያጋጥም ይችላል ነገር ግን በአልተመቸኝም ምክንያት የልጁን ብርሃን የሚያጨልም ወላጅ እንደሌለ ሁሉ የትውልድን ብርሃን ለማጨለም የሚወስን መምህር እንዳይፈጠር አደራ ብለዋል።

ዛሬ እንደ ሀገር በገባንበት ሁለንተናዊ ችግር የማይፈተን የለም የሚሉት ዶክተር ማተብ ሀገር በምትፈተንበት ወቅት ችግሩ የሚፈታውና ዘላቂ የሀገር ግንባታን ማንበር የሚቻለው ግን በትምህርት መኾኑን ተገንዝቦ ትምህርት ላይ አለመስነፍ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።

መንግሥት የትምህርት ዘርፉን ከስብራቱ ለማከም በትኩረት እየሠራ ስለመኾኑ ነው ዶክተር ማተብ የተናገሩት። በቀጣይ ትልልቅ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱንም አንስተዋል። ትምህርት ቤቶችን የማደስ፣ ከደረጃቸው የማሻሻል ትልቅ ተግባር ተይዟል ብለዋል።

በክልሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋትም በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል። “የትምህርት የመማር ማስተማር የባሕል ስብራቶችን መጠገን እንደሚስፈልግም አስረድተዋል። በዚህ ዓመት የመንግሥትን ትምህርት ቤቶች የቴክኖሎጅ እጥረት ለመመፍታት ልዩ ትኩረት ይሰጣል ነው ያሉት።

ንግግር እና ተግባርን ማገናኘት ነው ለውጥ የሚያመጣው የሚሉት ኀላፊው ሁሉም በኀላፊነቱ ለተግባር መነሳት እንደሚገባውም ተናግረዋል። የመምህራንን ቀን ስናከብር መምህራኖቻችን ለተሻለ ሙያዊ አበርክቶ፣ ሀገራዊ ኀላፊነትን በመወጣት ለትውልድ ግንባታ በልኩ እንዲሠሩ በማስብ ነው ያሉት ዶክተር ማተብ ቀኑ መምህራን የሚወሱበት፣ የታሪክ አሻራቸውን የሚያሳዩበት ቀን ነውና መምህራን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን ከጋምቢያና ማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ።
Next articleየመንግሥት ሠራተኞችን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉን ጤና ቢሮ ገለጸ።