
ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮ-ቱርክ የፓርላማ ወዳጅነት ቡድን የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር በሁሉም ዘርፍ የሕዝባቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው የፓርላማ ወዳጅነት ቡድን ከቱርክ አምባሳደር በኢትዮጵያ ጋር በሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ግንኙነት ዙሪያ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የኢትዮ-ቱርክ የፓርላማ ወዳጅነት ቡድን ሰብሳቢ የተከበሩ ፈቲህ ማህዲ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን እና የቱርክን ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በባሕል እና በቴክኖሎጅ ሽግግር በማጠናከር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የወዳጅነት ቡድኑ ዋና ዓለማ እንደሆነ የተከበሩ ዶክተር ፈቲህ አስገንዝበዋል።
የሁለቱን ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ቱርክ በአዲስ አበባ የባሕል ማዕከል ለመገንባት ፍላጎት እንዳላትም የተከበሩ ዶክተር ፈቲህ ጠቁመዋል፡፡
የወዳጅነት ቡድኑ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ቱርክ ከአፍሪካ ሀገራት በቀዳሚነት ኢምባሲዋን በኢትዮጵያ እንደከፈተች እና ሁለቱ ሀገራት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ የቱርክ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በሥራ ላይ ያሉትን እና ሥራ ያቆሙትን ኩባንያዎች በመለየት መፍትሄ ለማስቀመጥ በቀጣይ ከቱርክ አምባሳደር ጋር መመካከር አስፈላጊ እንደሆነ የወዳጅነት ቡድን አባላት አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ሚስተር በርክ ባራን የኢትዮጵያን እና የቱርክን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች የበለጠ ለማጠናከር በትብብር ለመስራት ቱርክ ፈቃደኛ መሆኗን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቱርክ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንትን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ችግሮችን በጋራ ፈትሾ ለማስተካከል እንመክራለንም ብለዋል።
በሌላ በኩል በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰበትን የአል-ነጃሽ መስጊድ ለመጠገን ቱርክ ፍላጎት እንዳለትም አምባሳደር በርክ ጠቁመዋል። መረጃው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!