500 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር እንትከል በሚል የሚካሄደውን ሥራ ለማሳካት የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ መሥሪያ ቤቶች ጋር እየሠራ መኾኑን ገለጸ፡፡

68

አዲስ አበባ: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ ፕሮግራምን አካሂዷል። በፕሮግራሙ ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ መሥሪያ ቤቶች ጋር በአረንጓዴ አሻራ ሥራ እና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መክሯል፡፡

በምክክሩ አረንጓዴ አሻራ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን የተፈጥሮ ሃብቶች ለመለወጥ ወሳኝ መኾኑ ነው የተገለጸው፡፡ በደን ጭፍጨፋ ምክንያት የመሬት መራቆት መከሰቱን ያነሱት ተወያዮቹ የአረንጓዴ አሻራ የደን መራቆትን በማስቆም ንፁህና ጤናማ አየር እንዲኖር ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቅሷል።

ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም 500 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር እንትከል በሚል የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ ተናግረዋል።

የተተከሉ ችግኞች ለውጥ እንዲያመጡም ክትትሎችን እንደሚያደርጉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ኢትዮጵያ ንፁህ አየር እንዲኖራት በማድረግ በዓለም ተመራጭ ሀገር ለማድረግ ሁሉም ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ራሄል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመምህራንን ቀን ማክበር ባለቤቶቹን ማውሳት፤ ሙያውንም ማጎልበት ነው” ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)
Next articleየኢትዮጵያ እና የቱርክ ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።