“የመምህራንን ቀን ማክበር ባለቤቶቹን ማውሳት፤ ሙያውንም ማጎልበት ነው” ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

51

ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ዓመታዊ የመምህራንን ቀን እያከበረ ነው።

መምሪያው ቀኑን አስመልክቶ መምህራን የሚወሱበት፣ የዓመቱ የደረጃ ተማሪዎች የሚበረታቱበት ፣ምስጉንና አንጋፋ መምህራን የሚመሰገኑበት፣ትምህርት ላይ ድጋፍ ያደረጉ አካላት ዕውቅናና ምስጋና የሚቸሩበትን ልዩ ፕሮግራም አዘጋጅቷል።

በመድረኩ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በዩኔስኮ የትምህርት ከተማ የተባለችው ባሕር ዳር ከተማ ለመምህራን ቀን የማይሳለስ ክብር እንዳላት አስታውሰዋል። ለትምህርት ዘርፉ፣ለተማሪዎቿና ለቀኑ ባለቤቶች ለመምህራን ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ነው የተናገሩት።

ዛሬ የምናከብረው የመምህራን ቀን ለመምህራን ለታሪካቸው ቅርስ የሚኾን ትውስታ የሚያገኙበት ነው ብለዋል። “የመምህራንን ቀን ማክበር ባለቤቶቹን ማውሳት ፤ ሙያውንም ማጎልበት ነው” ብለዋል ከንቲባው።

ዓለም በፈጣን የዕውቀት ሽግግር፣የሃሳብ ልእልና ላይ ናት ያሉት ዶክተር ድረስ ለውጥ እና ዕድገት በማያባራበት ዓለም የለውጥ ጥንስስ የሚጀመረው ትምህርት ቤት ነው ስለዚህ ትምህርትን መዘከር ፣ባለቤቶቹን ማውሳት፣ለሙያው ጉልበት ነውና ቀኑን ማክበር ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ቀኑን አስመልክቶ ባዘጋጀው ፕሮግራም የመምሪያው ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።

“የትምህርት አብርኆት” በሚል ርእሰ ጉዳይ “የትምህርት መነሻው፣መሄጃ መንገዱና መዳረሻው ” ያለውን ሂደት የሚያስቃኝ የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ ይቀርባልም ነው የተባለው። በተጨማሪም በከተማዋ በሚገኙ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል አንደኛ የወጡ ተማሪዎች ልዩ የዕውቅና ፕሮግራም ይደረጋል።

በመድረኩ ተማሪዎች፣ መምህራን ፣የትምህርት አካላትና ልዩ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ156 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታወቀ።
Next article500 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር እንትከል በሚል የሚካሄደውን ሥራ ለማሳካት የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ መሥሪያ ቤቶች ጋር እየሠራ መኾኑን ገለጸ፡፡