ከ156 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን የሰሜን ጎንደር ዞን አስታወቀ።

53

ደባርቅ: ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር እሸቱ መለሰ በደባርቅ ወረዳ የበለስ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ የጤፍ ማሳቸውን እያለሰለሱ ነው። ቀሪዎቹን ማሳዎቻቸውን ያገኙትን ማዳበሪያ ተጠቅመው በዘር ሸፍነዋል።
የዘሩት ሠብል ውጤት እንዲሠጥ ክትትል ያደርጋሉ። የደረሳቸውን የዩሪያ ማዳበሪያ ተጠቅመው ጤፍ ሊዘሩም ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

ሌላው የበለስ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ግርማይ አከወ ያገኙትን ማዳበሪያ ተጠቅመው መሬታቸውን በቀዳሚ ሰብሎች ሸፍነዋል። በየዓመቱ እስከ 12 ኩንታል ምርት የማምረት ልምድ አላቸው። ዘንድሮም የተሻለ ምርት ለማምረት አቅደዋል።
ዛሬም ሁለት ዕቃ በሬ ጠምደው የጤፍ ማሳቸውን ያለሰልሳሉ። የእርሻ ድግግሞሹ ለምርት መጨመር የሚኖረውን አስተዋጽዖ የተረዱ ይመስላሉ።
የደባርቅ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አድምጠው እባቡ በወረዳው 18 ሺህ 930 ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

ከ14 ሺህ 850 ሄክታር በላይ ማሣ በዘር መሸፈኑንም ጠቁመዋል።
በወረዳው ጤፍ፣ ስንዴ፣ የቢራ ገብስ እና ማሽላ የኮሚዲቲ ሰብሎች ተብለው የተለዩ ናቸው። ጤፍን ሳይጨምር ከ2 ሺህ 470 ሄክታር በላይ መሬት በ141 ክላስተር በመሥመር በዘር መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል።
የወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንደተናገሩት በወረዳው ፦

👉1 ሺህ 185 ኩንታል የስንዴ

👉260 ኩንታል የቢራ ገብስ

👉184 ኩንታል የጤፍ ምርጥ ዘር ቀርቧል፡፡

በአጠቃላይ 441 ሺህ 540 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ የታቀደ ሲኾን ከዚህ ውስጥ 163 ሺህ ኩንታል በላይ ከኮመዲቲ ሰብሎች የሚገኝ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ በዞኑ ከ156 ሺህ 659 ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱን ተናግረዋል። እስካሁን 125 ሺህ 570 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም አንስተዋል። በሥራው ላይ 182 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደተሳተፉም አስታውቀዋል።

እስካሁን በሰብል ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 37 ሺህ 28 ሄክታር መሬት በመሥመር መዘራቱም ነው ያነሱት። በመሥመር መዝራት ሥራው ላይ ከ87 ሺህ 413 በላይ አርሶአደሮች ተሳትፈዋል።
በዞኑ 33 ሺህ ሄክታር መሬት በስድስት ኮሞዲቲ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዷል፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 17 ሺህ 412 ሄክታር መሬት በሰለጠኑ አርሶ አደሮች በዘር መሸፈኑን አንስተዋል።
አቶ ጌታቸው በዞኑ ምርታማነትን ለመጨመርም፡-

👉23 ሺህ 967 ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በአዲስ የቀረበ ሲኾን

👉18 ሺህ 730 ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል

👉በድምሩ 42 ሺህ 697 ኩንታል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉንም አንስተዋል፡፡

👉2 ሚሊዮን 116 ሺህ 493 ሜትሪክ ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ስለመዋሉም አስረድተዋል።

የዞኑን ምርት ለማሳደግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ሲኾን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በካይሮ ተወያዩ።
Next article“የመምህራንን ቀን ማክበር ባለቤቶቹን ማውሳት፤ ሙያውንም ማጎልበት ነው” ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)