
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ምክር ቤቱ ባከወናቸው ጉዳዮች ዙሪያና ቀጣይ የሚካሄደውን ጉባዔ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የአማራ ክልል መንግሥት ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከሐምሌ 12 እስከ 14/2015 ዓ.ም እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱ ከሕዝብ በሚመነጩ አጀንዳዎች ላይ በመመስረት ይመክራል ነው የተባለው። በምክር ቤቱ ጎላ ብሎ የሚነሳውና የሚመከርበት የሕዝብ ጥያቄ ነው ተብሏል። የሕዝብ ጥያቄዎች በምክር ቤቱ በስፋት ይመከርበታል። የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ እንዲከበር ምን መደረግ አለበት፣ ምክር ቤቱ ምን መሥራት አለበት የሚለውን በሥፋት ይመክርበታል ነው የተባለው።
ምክር ቤቱ ሕግ ማውጣት፣ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ዋና ዋና ተግባራቱ መኾኑን ያነሱት አፈ ጉባዔዋ በምክር ቤቱ ሁለቱ ጉዳዮች በትኩረት ይታያሉ ነው ያሉት። ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ 6 አዋጆችን ማውጣቱንም አንስተዋል። ምክር ቤቱ አሥፈፃሚ አካላት በእቅዳቸው መሠረት የፈፀሙትን ቁጥጥር እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።
ባለፉት ዓመታት የነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዴት ተመልሰዋል የሚለውን እንደሚያዩም አስረድተዋል። የታቀዱ እቅዶች እንዴት እየተፈጸሙ እንደኾነ እንደሚመከርበትም ተናግረዋል።
ውክልናን በአግባቡ የመወጣት ተግባር ሌላኛው የምክር ቤቱ ስልጣን እና ተግባር መኾኑንም አንስተዋል። ተመራጮች የመረጣቸውን ሕዝብ እንደሚያገኙና ከሕዝብ ጋር ምክክር እንደሚያደርጉ ያነሱት አፈጉባዔዋ በርከት ያሉ የመራጭ ተመራጭ መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል። ተመራጮች የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። በዓመቱ ከሕዝብ የተነሱ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ መሠራቱንም ተናግረዋል።
ተመራጮች ከመራጮቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በክልሉ ሰላም እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ በሕዝብ በዋናነት የተነሱ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል። ከዚህ ባለፈ የልማት ጥያቄ በሕዝብ የሚነሳ መኾኑን አንስተዋል። ምክር ቤቱ በነፃ የስልክ መስመር ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን እንደሚቀበልም አንስተዋል። ጥያቄዎቹም በክልሉም፣ ከክልሉም ውጭ ካሉ ዜጎች የሚመጡ ናቸው ተብሏል።
ምክር ቤቱ በ6ኛ መደበኛ ጉባዔው የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን መርምሮ ያፀድቃል። የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ይመክራል ተብሏል። ምክር ቤቱ በሚኖረው ጉባዔ አዋጆችን መርምሮ ያፀድቃል፣ የክልሉን የ2016 በጀት መርምሮም ያጸድቃል፤ ሹመትና ልዩ ልዩ ጉዳዮች ይኖራሉም ብለዋል። ሕዝቡ በምክር ቤቱ እንዲነሱ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች በ888 ነፃ የስልክ መሥመር እንዲያደርስ ዋና አፈጉባዔዋ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!