
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው። ቋሚ ኮሚቴው ከሚከታተላቸው ተቋማት ውስጥ መሬት ቢሮ አንዱ ነው። ቢሮው የ2015 በጀት ዓመት ዓበይት ክንዋኔዎችን እና የገጠሙትን ተግዳሮቶች ለምክር ቤቱ አቅርቧል። የክልሉ መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ለልማት ሥራዎች መሬታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ እና ፈጣን ካሳ አለማግኘታቸው የበጀት ዓመቱ አንዱ ተግዳሮት ነበር ብለዋል።
እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ በበጀት ዓመቱ 21 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለልማት ተነሽዎች ካሳ ለመክፈል ቢታቀድም እስከአሁን 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው መክፈል የተቻለው። ለልማት ተነሽዎች መከፈል የነበረበት 12 ነጥብ 1 ቢሊዮን የካሳ ግምት ብር ገና ያልተከፈለ መኾኑንም አንስተዋል። ካልተከፈለው የካሳ ግምት ውስጥ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን የሚኾነው ካሳ በፌደራል መንግሥት ለሚከናዎኑ የልማት ሥራዎች መሬታቸውን ለለቀቁ አርሶ አደሮች መከፈል የነበረበት ስለመኾኑም ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል።
ከተሜነት እየሰፋ ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው መስፋፋቱ ከይዞታ መሬታቸው የሚያስነሳቸው አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ካሳ ተገምቶላቸው በወቅቱም እንዲያገኙ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አንስተዋል።
ሕገወጥ የመሬት ወረራን ለመቆጣጠር የአመራሩ ቸልተኝነት፣ የከተማ መሬት መረጃን ለማዘመን ትኩረቱ አነስተኛ መኾን እና 2ኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ለመስጠት በፍትሕ ተቋማት ላይ የገጠመው የግንዛቤ ክፍተት የበጀት ዓመቱ ተግዳሮቶች ነበሩ ተብሏል።
ቢሮው የክልሉ 113 ወረዳዎችን ወደ ብሔራዊ የመሬት መረጃ አሠራር እንዲገቡ ማድረጉ እንደ ጥንካሬ ተነስቷል። የከተማ መሬት በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ተመዝግቦ እንዲያዝ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ዘመናዊ የመሬት መረጃ ሥርዓቱ ከመሬት አስተዳደር ሥርዓት ጋር በተያያዘ ይፈጸሙ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችን በመቀነስ ውስን የኾነውን ሃብት ከሕገወጦች ለመከላከል አጋዥ ስለመኾኑም በውይይቱ ተነስቷል።
የአርሶ አደሮች መሬት ለልማት ሲፈለግ ቅድሚያ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ሳይከናወንና በቂ ካሳ ሳይከፈል የመውሰድ ችግር ትኩረት የሚሻ ስለመኾኑ በምክር ቤቱ ተነስቷል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!