የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በምሁራን አንደበት፡፡

183
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 07/2012ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በ1987 ዓ.ም የበኩር ጋዜጣን ማሳተም ጀምሮ ወደ ብዙኃን መገናኛ ኢንዱስትሪ የተቀላቀለ የሜዲያ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ባለፉት 25 ዓመታት በጋዜጦች፣ በቴሌቭዥን፣ በ ኤፍ ኤሞችና መካከለኛና አጭር ሞገድ ሬዲዮ እንዲሁም በማኅበራዊ ገጾች የተለያዩ መረጃዎችን ለአንባቢያንና አድማጭ ተመልካቾች በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ ብዙኃን መገናኛው ዘመኑ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች በመታጠቅ በዚህ ወቅት በአምስት የተለያዩ ቋንቋዎች መረጃ ለተደራሲያን በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡

ከዛሬ ታኅሳስ 7 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ለተከታታይ ሳምንታት የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን ማክበር ጀምሯል፡፡ 25ኛውን ዓመት እስካሁን ይዞ የመጣቸውን ጥንካሬዎች እና መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች በተመለከተ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አቶ ካሱ ኃይሉ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ (ምጣኔ ሀብት) መምህር ናቸው፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትን ለዓመታት በቴሌቭዥን፣ ሬዲዮ እና በጋዜጦች በሚያቀርባቸው መረጃዎች እንደሚከታተሉም ተናግረዋል፡፡ አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ማኅበረሰቡ በምጣኔ ሀብት፣ በፖለቲካ ብዝኃነት፣ በባሕል፣ በስፖርት፣ በኪነ-ጥበብ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋጾ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስተያዬት ሰጭዎቹ ተናግረዋል፡፡ ከመጣበት ጎዞ በበለጠ ደግሞ ወደፊት ብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ ራሱን አዘምኖ ‹‹እንዴት የሕዝብ ድምጽ መሆን እችላለሁ?›› በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበት መክረዋል፡፡ ብዙኃን መገናኛ የመንግሥት የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ከመሆን ይልቅ የተለያዩ ሐሳቦች የሚንጸባረቁበት፤ ባለሙያዎችም ሕግ የሚፈቅድላቸውን ነፃነት በመጠቀም ተግባራዊ ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

‹‹የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሻሻሎችን እያሳየ መሄዱን እገነዘባለሁ›› ያሉት መምህሩ ብዙኃን መገናኛው ተጠያቂነትን፣ ሚዛናዊነትን እና ሌሎች ሙያዊ መርሆዎችን ተከትሎ መሥራት እንዳለበትም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

‹‹የብዙኃን መገናኛ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና ደጋፊ ባለሙያዎች የሙያ ብቃታቸውን በየጊዜው እያሻሻሉ መሄድ ይኖርባቸዋል፤ ይህም ሲሆን ጩኸቶችን ከማስተጋባት ባሻገር በዕውቀት ወደሚመራ ዘገባ፣ የምርመራ ጋዜጠኝነት፣ ጽንሰ-ሐሳባዊ ትንተና እና ወደ መሠረታዊ የለውጥ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ያግዛቸዋል›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡ በዚህ ረገድ አብመድ ማሻሻል ያለበት ጉዳይ እንደሚኖርም አስረድተዋል፡፡ አብመድ የአማራን ሕዝብ የስበት ማዕከሉ በማድረግ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ ቱሪዝምን በማስፋፋት፣ ሙስናን በመዋጋት፣ መሠረተ-ልማትን በማሳደግ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ረገድ ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚገባም አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል ምሁሩ፡፡

‹‹አብመድ ዓለም አቀፋዊ ራዕይ ሊሰንቅ ይገባዋል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ አንድ ትልቅ የብዙኃን መገናኛ አማራጭ ሆኖ ስለመውጣት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የረጅም ዓመት ስትራቴጂክ (ስልት) ዕቅድ ቀርፆ መንቀሳቀስ እንዳለበት አስባለሁ፡፡ ለዚህም በመረጃ ጥራት፣ በተደራሽነት፣ ቋንቋዎችን በማስፋት እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ሥራ ያስፈልገዋል›› ብለዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ሰይድ መሐመድ ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሀገራዊ ለውጡ ያበረከተው አስተዋፆ ጉልህ እንደነበር አውስተዋል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፍም የአውራምባ ማኅበረሰብ ለዓለም እንዲተዋወቅ የተወጣውን ጉልህ ሚና እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡
እርሳቸውም በአብመድ የአውራምባን ማኅበረሰብ በቴሌቪዥን መስኮት ከተመለከቱ በኋላ በቦታው በመገኘት ጥናት ማካሄዳቸውን አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎችን የሥራ እንቅስቃሴ፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲጠናከር እና የተለያዩ ሥራዎችን ለሕዝቡ ጆሮ እና ዓይን ለማድረስ እያደረገ ያለውን ግብግብ አጠናክሮ መሄድ እንዳለበትም አብራርተዋል ረዳት ፕሮፌሰር ሰይድ፡፡

25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር ደግሞ ጋዜጠኞች ተሟጋች እንዲሆኑ እና ራሳቸውን በዕውቀትም ሆነ በክህሎት ማብቃት ስላለባቸው አንባቢ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ ‹‹የጤናን መርሀ ግብር ብቃት ያለው የጤና ባለሙያ ጋዜጠኛ ሆኖ ቢያቀርብ ሙሉ መረጃ ይሰጣል፤የፖለቲካውን ዘርፍም እንደዚሁ›› ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር ሰይድ፡፡

አቶ አምሳሉ ንጋቱ ደግሞ በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ተቋም የአዴት የምርምር ማዕከል የግብርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ ስለአብመድ ሥራዎች ሲገልፁ ‹‹በአጠቃላይ ስለሚቀርቡ መርሀ ግብሮች አስተማሪና ወቅታዊነታቸው አዎንታዊ አስተያየት ነው ያለኝ›› ብለዋል፡፡ ይህ ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ጊዜ በኅብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ የፈጠሩ ክስተቶችን ከሁሉም አቅጣጫ በማቅረብ ረገድ እጥረት እንደሚታይበት እና መሻሻል እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

ያለንበት ጊዜ መረጃዎች በተለያዩ የትስስር መንገዶች በፍጥነት ወደ ሰው ጆሮ እና ዓይን የሚደርሱበት ወቅት ስለሆነ እውነተኛውን መረጃ ከምንጩ በአፋጣኝ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት መሻሻል እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡

‹‹በሚቀርቡ መርሀ ግብሮች ላይ የሚሳተፉትና ማብራሪያ እንዲሰጡ የሚጋበዙ ግለሰቦችም የሥራ ኃላፊዎች ብቻ ባይሆኑ ይመረጣል፤ ብዙኃን መገናኛው የሁሉም ሀብት እንደመሆኑ መጠን ሁሉም መነጋገር አለበት›› ብለዋል አቶ አምሳሉ፡፡

አብመድ በኩር ጋዜጣን በሳምንታዊ ጋዜጣነት ማሳተም የጀመረበትን ታኅሳስ 07 ቀን 1987ዓ.ም እንደ መነሻ በማድረግ ዛሬ የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን እያከበረ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous article‹‹ከለውጡ በኋላ ይታዩ የነበሩት የድርጅቱ ጠንካራ ዘገባዎች እየተቀዛቀዙ ነው፡፡›› የአብመድ አድማጭ ተመልካቾች
Next articleየአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት የሥራ ኃላፊዎች የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ ሰጠ።