በዞኑ ከ1ሺህ 700 በላይ ለኾኑ አረጋውያንና በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለኾኑ ግለሰቦች ቤታቸው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕድሳትና ግንባታ ሊደረግላቸው ነው፡፡

30

ደሴ: ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ከ1ሺ 700 በላይ የአረጋውያንና የአቅመ ደካማ ቤቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ መልክ እንደሚሠሩና እድሳት እንደሚደረግላቸው ነው የተገለጸው፡፡ በዞኑ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራም በተሁለደሬ ወረዳ ሱሉላ ቀበሌ ዛሬ ተጀምሯል፡፡

በተሁለደሬ ወረዳ ሱሉላ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት በላይ ይመር ቤት ንብረታቸው በጦርነት ወድሞባቸው ከጎረቤት ተጠግተው ሕይዎትን በአስቸጋሪ ሁኔታ ሲገፉ ቆይተዋል፡፡ ግለሰቧ ዛሬ በተጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው እንደ አዲስ መሠራት በመጀመሩ መደስታቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡አስታዋሽ በማግኘታቸውም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

በዞኑ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ587 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የተናገሩት የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጀማል ሞላ በአገልግሎቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በሥራውም ፡-

👉1 ሺህ 160 ቤት እድሳትና ጥገና

👉581 አዲስ ቤት ግንባታ

👉2 ሺህ 596 ዩኒት ደም ማሰባሰብ እንዲሁም

👉134 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ በበጎ ፍቃደኞች ይከናወናል ነው ያሉት።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው በጦርነቱ የወደሙትን ጨምሮ የገንዘብ አቅማቸው ደካማ የኾኑ ነዋሪ ቤቶችን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሥራትና ለመጠገን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የሰው ልጆች ላይ ትኩረት መደረጉ ለሕዝብ ያለንን ትኩረት ማሳያ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር በበኩላቸው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የልማት ተደራሽነት ክፍተትን ከመሙላት ባለፈ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እያቃለለ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበጋ መስኖ ልማት የምርት ስብሰባ እያከናወነ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።
Next articleአቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ ላይ ለመሳተፍ ኬንያ ገቡ።