የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የዓመቱን ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት አቀረበ፡፡

70

አዲስ አበባ: ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይፋ ያደረገው ሪፖርት ከሰኔ/ 2014 ዓ.ም እስከ ሰኔ/2015 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው፡፡

ኮሚሽኑ ባደራጃቸው ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች እና የከተማ ጽሕፈት ቤቶች አማካኝነት በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን የሚዳስስ ሪፖርት ነው ያቀረበው።

ሪፖርቱ ኮሚሽኑ ቀደም ሲል በለያቸውና በሚሠራባቸው የትኩረት ዘርፎች ላይ መሠረት ያደረገ እንደኾነም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ.ር) በሪፖርታቸው ካቀረቡት በዓመቱ ከተመዘገቡ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን ማሻሻል የሚያስችሉ ቁልፍ ክስተቶች እና እመርታዎች መካከል፡-

👉በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ በጥቅምት/2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የዘላቂ ተኩስ ማቆም እና ሰላም ስምምነት መፈረሙ

👉የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ባደራጀው የባለሙያዎች ቡድን ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮች ማዘጋጀቱ እና ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች መካሄድ መጀመራቸው

👉በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል አብዛኛው አካባቢዎች ሰላም የሰፈነ መኾኑ

👉በተወሰነም ደረጃ የሚታዩ የመልሶ ግንባታ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መሻሻል፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ጥረቶች መጀመራቸው እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል፡፡

በኮሚሽኑ ክትትል እና ምክረ ሐሳብ መሠረት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በፈጸሙ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ረገድ በሁሉም ክልሎች የሚታዩ ጅማሮዎች አበረታች መኾናቸውን ነው ዶክተር ዳንኤል ያስገነዘቡት፡፡

ኮሚሽኑ በሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች መሠረት ለእስር ወይም ለአስገድዶ መሰወር የተዳረጉ ሰዎች ሲፈቱ፣ አቤቱታ ያቀረቡ ሰዎች እልባት ሲያገኙ እንዲሁም አሠራሮች ሲዘረጉ እና የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያ ሥራዎች ሲጀመሩ ታይተዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዲስ አበባ ከተማ የ109 የአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሥራ ፈቃድ ተሰረዘ፡፡
Next articleየበጋ መስኖ ልማት የምርት ስብሰባ እያከናወነ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።