
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ውኃ ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው። ቋሚ ኮሚቴው ከሚከታተላቸው ተቋማት ውስጥ ግብርና ቢሮ አንዱ ነው። ቢሮ ኀላፊው ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) የ2015 በጀት ዓመት ዋና ዋና ስኬቶች እና ተግዳሮቶችን የተመለከተ ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
ዶክተር ኃይለማርያም የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እና የአቅርቦቱ መዘግየት የግብርናው ዘርፍ ተግዳሮቶች ስለመኾናቸው ለቋሚ ኮሚቴው አንስተዋል። የችግሩ ምንጭም እንደ ሀገር የገጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ስለመኾኑ ተናግረዋል። የገጠመውን እጥረት እንደ ምቹ ኹኔታ በመጠቀም የአፈር ማዳበሪያን በሕገ ወጥ መልኩ ለማዘዋወር የሚሞክሩ ሕገ ወጦችን የመቆጣጠር በትኩረት ሲሠራ መቆየቱንም ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል።
ከሕገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ በ39 ወረዳዎች 259 ግለሰቦች ሲሳተፉ የተደረሰባቸው ሲኾን 3 ሺህ 942 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተነግሯል። ዶክተር ኃይለማርያም የገጠመውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረትን ቀድሞ በመረዳት በተደረገው ንቅናቄ 77 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች አቅም ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል።
የስንዴ ግብይት በሚፈለገው አግባብ አለመኾን፣ የዘር ብዜት መሬት እጥረት፣ ለሌማት ቱሩፋት የሚያስፈልግ ግብዓት እና ቴክኖሎጅ እጥረት እና በጦርነት ምክንያት በርካታ የግብርና መሰረተ ልማቶች መውደማቸው በበጀት ዓመቱ በግብርናው ላይ የታዩ ችግሮች ስለመኾናቸውም ለቋሚ ኮሚቴው ተነስተዋል።
የእርሻ ሜካናይዜሽን፣ የተሻለ የበጋ ስንዴ ልማት፣ ክልሉ በምርጥ ዘር ብዜት ራሱን መቻሉ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ውጤታማነት እንዲሁም የተሳካ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅት የቢሮው መልካም ተሞክሮዎች ነበሩ ተብሏል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!