‹‹ከለውጡ በኋላ ይታዩ የነበሩት የድርጅቱ ጠንካራ ዘገባዎች እየተቀዛቀዙ ነው፡፡›› የአብመድ አድማጭ ተመልካቾች

199

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 06/2012ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የዛሬ 25 ዓመታት በበኩር ጋዜጣ አማካኝነት ለኅብረተሰብ ለውጥ መሥራት ጀምሯል፡፡ ታህሣስ 7/1987 ዓ.ም በበኩር ጋዜጣ አማካኝነት የአርሶ አደሩ ምርታማነት ለመጨመር፣ ኢንዱስትሪ ሽግግሩ እንዲፋጠን፣ የከተሞች ሕይወት ጤናማ እና ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን፣ ሕዝቡ ከብልሹ አሠራሮች ለመታደግ፣ መሪዎችን ኃላፊነት የተሞላበት ሥራ እንዲሠሩ በማመላከት 25 ዓመታትን አገልግሏል፡፡

ግንቦት 16 ቀን 1989 ዓ.ም በኢትዮጵያ ክልሎች በራዲዮ ስርጭት ጅማሮ የቀዳሚነት ምዕራፍን የገለጠው አማራ ራዲዮ ነው፡፡ ሚያዝያ 1992 ዓ.ም የአማራ ብሔራዊ ክልል የቴሌቪዥን ኘሮግራም ለአየር በቃ፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የፌስ ቡክ ገጽም 2004 ዓ.ም ጅማሮውን አደረገ፡፡ አሁን ሁሉም የብሮድካስት ሚዲየሞች ከ30 ደቂቃ የአየር ሰዓት ጀምረው ከንጋት እስከ ንጋት ደርሰዋል፡፡

በአማርኛ፣ ኽምጠኛ፣ አዊኛ፣ ኦሮምኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አድማጭ ተመልካቹን በሚቻለው ሁሉ በለውጥ ለማሻገር ጥረት አድርጓል፡፡ የ25 ዓመት የብር ኢዮቢልዩ በዓሉን ታኅሳስ 07/2012 ዓ.ም ለማክበር እየተዘጋጀ የሚገኘው ድርጅቱ አድማጭ፣ ተመልካች እና አንባቢዎች የሚዲያው አካል በመሆናቸው ጠንካራና ደካማ ጉኑን እንዲነግሩት ሐሳብ ሰብስቧል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ ወርቅነህ ጋሻው አብመድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በየዞኑ ዘጋቢዎችን በመመደብ በየወቅቱ ያሉ መረጃዎች እንዲሠሩ የተጀመሩ ጥረቶች ጥሩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከዋና መቀመጫው ባሕር ዳር ባሻገር በየዞኖች የተደራጀ የሰው ኃይል በመመደብ ሕዝቡን በቅርበት በማገልገሉ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል›› ብለዋል፡፡ ‹‹በይዘት አመራረጥ እና በወቅታዊነት ቀዳሚ ጣቢያ ነው›› ያሉት አቶ ወርቅነህ የቴሌቭዥን ጣብያው ላይ የሚያደርገው የመገኛ ሞገድ (ፊሪኩየንሲ) መቀያየር ግን እንዳስቸገራቸው ገልፀዋል፡፡

የአብመድ የኤፍ ኤም እና የቴሊቪዥን ጣብያዎች ቀዳሚ የመረጃ ማዕከሎች ናቸው ያሉት ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ እማዋይሽ በላይ ናቸው፡፡ ‹‹ጣብያው የሚያስተላልፋቸው መርሀ ግብሮች አብዛኛዎቹ ከቀልድና ዋዛ ፈዛዛ ይልቅ አስተማሪ ጉዳዮች ላይ በማተኮሩ ምርጫየ ነው›› ብለዋል፡፡ ወቅቱን ያማከሉ መረጃዎችን በስፋት እና በትንታኔ ማቅረብ መቻሉም ጠንካራ ጎኖች ናቸው ብለዋል፡፡

ሌላው የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ አበበ ቸኮል ‹‹አብመድ ታማኝ እና ሚዛናዊ የመረጃ ምንጭ ነው›› ብለዋል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት የነበረው ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እና ቀዳሚነቱ አሁን ላይ እየቀዘቀዘ በመሆኑ ዳግም ራሱን ሊፈትሽ ይገባዋል›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ድርጅቱ አሁንም የአማራ ክልል ሕዝቦች አንደበት እና የመማማሪያ ማዕከል እንዲሆን በየዞኑ ዘጋቢዎችን በመመደብ በቅርበት መሥራት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

በደብረ ብርሃን ከተማ ቀበሌ 07 ነዋሪ የሆኑት አቶ ግዛቸዉ ምሕረቴ ደግሞ ‹‹ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የበኩር ጋዜጣን ጨምሮ የአብመድ ሥራዎችን እከታተላለሁ። ከማኅበራዊና ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በግልጽ የማሳወቅ ጉድለት ነበረበት። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር በተገናኘ በኩር ጋዜጣ ተደጋጋሚ ይዘት ያላቸዉ ርዕሰ ጉዳዮችን ያወጣ ነበር። አብመድ የአማራ ሕዝብ ፍላጎት ለይቶ በመታገል በኩል አልሠራም። አድርግና ጻፍ የተባለዉን የሚተገብር ድርጅት እንደነበር ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አብመድ ወሳኝ የሕዝብ ልብ ትርታ በማዳመጥ ችግሮች ምላሽ እንዲሰጥባቸዉ አድርጓል›› ብለዋል።

አስቀድሞ መረጃ እንደሚሰጥም ገልጸዋል። በቀጣይ ባለስልጣናትና ዉሳኔ ሰጪ አካላት ለአማራ ሕዝብ ለዉጥ፣ ዕድገትና ልማት የድርሻቸዉን እንዲወጡ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀውም አመልክተዋል። ከብልሹ አሠራርና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የተያያዙ ተግባራትን እያጋለጠ የክልሉን ልማት ማፋጠንና መደገፍ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የደብረ ብርሃን ቀበሌ 05 ነዋሪው አቶ ሸጋዉ ወርቁ ደግሞ ሬድዮ ስርጭቱን እንደሚከታተሉ ነግረውናል። ‹‹አብመድ የመንግሥት መዋቅር ላይ ያሉ መስሪያ ቤቶች በመፈተሽ ችግሮች እንዲቀረፉ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው›› ብለዋል። በቀጣይ ሀገራዊ ዘገባዎችን በብዛት ሊያሰማ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በክልሉ ውስጥ ብቻ መታጠር እንደሌለበትም ነው ያስገነዘቡት።
የደብረ ብርሃን ከተማ ቀበሌ 09 ነዋሪው ማሞ ብሩ እንዳሉት ደግሞ አብመድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከለውጡ በኋላ በተሻለ ሁኔታ የተንቀሳቀሰና ራሱን ማሳወቅ የቻለ ድርጅት ነው። ‹‹አቋሙ መጠንከር አለበት፤ በያዝ ለቀቅ እየተጓዘ ነው። በቀጣይ ወጣቱን ከሱስ አቅቆ እንዲደራጅ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል›› ብለዋል።

ዘመድኩን ግዛዉ የተባሉ የአብመድ ተከታታይ ደግሞ ‹‹ስለሁሉም ርዕሰ ጉዳዮች መረጃ እንዲኖረን ያደርጋል። የመንግሥት የታችኛውን የአደረጃጀት መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ ወርዶ በመፈተሽና ዘገባ በመሥራት፤ የየትኛውንም የአማራ ክልል አካባቢ ተደራሽ ማድረግ ላይ የሚቀር የቤት ሥራ አለ። በደረሰበት ልክ ግን አብመድ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ክስተትና እውነት ያስተላልፋል›› ብለዋል።

ማንነታቸዉን መግለጽ ያልፈለጉ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሁለት ሴት ተማሪዎች ደግሞ ‹‹ሀቀኝነቱና እውነታን መናገሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት›› ብለዋል።

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የአማራ እሴቶችን አንግቦ፣ የሕዝቡ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ትውፊቶች እንዲጎለብቱ የሚያስችሉ የዜናና የመርሀ ግብር አጀንዳዎችን ቀርፆ እንደሚሠራ ይታወቃል፡፡ አብመድ ኅብረተሰቡ ሚዲያው እንዲጎለብት የሰጠውን ሐሳብም ከ25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ ጋር አያይዞ ለለውጥ መነሻ ጥቅም ላይ እንደሚያውለው ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ እና ኪሩቤል ተሾመ

Previous articleየኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጀመራል፡፡
Next articleየአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በምሁራን አንደበት፡፡