“ነጻነት ተፈጥሯዊ መብት ነው፤ የተነጠቅነውም ያስመለስነውም ተፈጥሯዊ መብታችንን ነው” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ

81

ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሐምሌ 5 እስከ ጥቅምት 24 በሁለት የተለያዩ ዓመታት ያየናቸው ሁለት ዓበይት ክስተቶች የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ትግል እና ድል ፈር ያስያዙ አጋጣሚዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

ዴሞክራሲያዊ ጥያቄን በሰከነ እና በሰለጠነ መንገድ መመለስ ያልቻሉ የዓለም አምባገነን መንግሥታት ያዩትን ውርደት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ትናንት የነበሩ አምባገነኖችም አይተዋል፡፡

ትውልዱ ከሀገር እና ሕዝብ በላይ የኾነ ፍጹም ምድራዊ ኃይል እንደሌለ በዚያች ተዓምራዊት ሌሊት በተግባር አይቷል፡፡ ግፈኞች የግፍ ቁናቸው ሞልቶ የሚያፈሰውን መከራ እና ሞት መቀበል ጀምረዋል፡፡ ሐቅን እስከ ህቅታ የያዙ እውነተኛ የሕዝብ ልጆች ደግሞ ለአይቀሬው ድል የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም እውነት እስከ ንጋት ድረስ ሳትጠበቅ ሕዝብ አሸናፊ የኾነበትን የድል ብስራት ዜና ሐምሌ 5 ምሽት ላይ ሰማ፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊም ኾነ ጥንታዊ የሀገረ-መንግሥት ምስረታ ታሪክ የአማራ ሕዝብ ታላቅ አበርክቶ አለው ያሉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኅላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የታላቅ አበርክቶው መገለጫ ራሱን በንቃት ከመጠበቁ እና የሌሎችንም አጥብቆ ከማክበሩ ይመነጫል ይላሉ፡፡ በየዘመኑ ያለፈው ሥርዓተ መንግሥት ሁሉ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ከሕዝብ ተጠቃሚነት አንጻር ሲታይ በርካታ ክፍተቶች ነበሩበት የሚሉት ኮሎኔል ደመቀ ባለፈው ሥርዓት ከነበረው ዝቅጠት የከፋ ክስተት የታየበት ጊዜ ግን አልነበረም ይላሉ፡፡

ባለፈው ሥርዓት የአማራ ሕዝብ ማንነቱ ተጨፍልቆ፤ ነጻነቱን ተነጥቆ ቆይቷል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ከበርካታ ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ በቅርቡ ማንነቱንም ፤ ነጻነቱንም ማስመለስ ችሏል ነው ያሉት፡፡ ያስመለሰውን ነጻነት አስጠብቆ እና ማንነቱን ጠብቆ ለመዝለቅ ከምንጊዜውም በላይ በሰከነ እና በበሰለ መንገድ መጓዝን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ “ነጻነት ተፈጥሯዊ መብት ነው፤ የተነጠቅነውም ያስመለስነውም ተፈጥሯዊ መብታችንን ነው” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ከነጻነት ማግስት ለመልማት እና ለማደግ መሥራት ደግሞ ሌላው ተፈጥሯዊ ግዴታችን መኾን አለበት ብለዋል፡፡ ዞኑ በሙሉ አቅሙ እና ትኩረቱ ልማት ላይ መኾኑን በማንሳት፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ እና አሥተዳደር ከነጻነት ማግስት ጀምሮ በሰላም ማስጠበቅ እና በልማት ሞዴል አካባቢ ኾኗል ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና አንጻራዊ መረጋጋት ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አንዱ ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ የተገኘው ሰላም የሕዝቡ እና አሥተዳደሩ መናበብ እና መደጋገፍ የፈጠረው ጥምረት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ላለፉት ዓመታት ለማንነቱ እና ለነጻነቱ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ በመኾኑ ያገኘውን ድል ለማጽናት በቁርጠኝነት እየሰራ መኾኑን ያነሱት ኮሎኔል ደመቀ የአማራ ሕዝብ ካለፈው መማር፣ አንድ መኾን እና ለዓላማ መጽናት ግድ የሚልበት ወቅት ላይ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ትግል ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያይ መኾን ይኖርበታል ያሉት መምሪያ ኅላፊው ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ለነገ የማይባል የአማራ ሕዝብ የቤት ሥራ እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከተሞቻችን የነጻነት ብቻ ሳይኾን በራስ አቅም የመልማትም ተምሳሌት ኾነዋል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ
Next articleትናንት ምሽት በሀገሪቱ በረካታ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረው የኃይል አቅርቦቱ ወደነበረበት ተመልሷል።