“ከተሞቻችን የነጻነት ብቻ ሳይኾን በራስ አቅም የመልማትም ተምሳሌት ኾነዋል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ

35

ሁመራ: ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የተለያዩ ከተሞች ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ በኀብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በቅርቡ ይመረቃሉ ተብሏል፡፡ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ የጎርፍ መከላከያ፣ ድልድይ እና የሕዝብ ቤተ መጽሐፍ ግንባታዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ናቸው ተብሏል፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከነጻነት ማግስት በውስጥ አቅም እና በኀብረተሰብ ተሳትፎ በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ዞኑ ከበርካታ ዓመታት እልኽ አስጨራሽ ትግል በኋላ ወደ ቀደመ ማንነቱ መመለሱን ተከትሎ ሕዝቡ ከነጻነት ማግስት ወደ ተለያዩ የልማት ሥራዎች ሲገባ ጊዜ አልወሰደም፡፡ በቅርቡ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ከውስጥ አቅም፣ ከዞኑ ነዋሪዎች እና በውጭ ከሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ድጋፍ በተገኘ ገንዘብ የተገነቡ በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚኾኑ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ኅላፊ አቶ ዓለሙ አወቀ በተለይም ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

ለምረቃ ለአገልግሎት ዝግጁ ናቸው የተባሉት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በቃፍቲያ ሁመራ፣ ወፍ አርግፍ እና ዳንሻ ከተሞች የተገነቡ ናቸው ተብሏል፡፡ የቃብቲያ ወረዳ መቀመጫ የኾነችው የአዲ ኽርዲ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን አጠናቅቋል ያሉት አቶ ዓለሙ የጎርፍ መከላከያ፣ የጌጠኛ መንገድ ግንባታ፣ የጠጠር መንገድ ግንባታ እና የቤተ መጽሐፍት ግንባታዎች ተጠናቀዋል ነው ያሉት፡፡

መሪ ማዘጋጃ ቤቱ ገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ካደረጋቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በተጨማሪ ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠርም መልካም የሚባል ጅማሮን አሳይቷል ተብሏል፡፡ በአንድ የአካባቢው ተወላጅ ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ተገንብቶ ለአግልግሎት የተዘጋጀ ቤተ መጽሐፍት ይመረቃል ያሉት አቶ ዓለሙ ቤተ መጽሐፍቱ ኮምፒውተርን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችም ተሟልተውለታል ተብሏል፡፡

በወልቃይ ወረዳ የወፍ አርግፍ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤትም በ2015 ዓ.ም በውስጥ ገቢ እና ከሕዝብ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተከናውነው ለምረቃ ዝግጁ ናቸው ተብሏል፡፡ መሪ ማዘጋጃ ቤቱ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የከተማ አሥተዳደሩን ሕንጻ ገንብቶ አጠናቅቋል ያሉት አቶ ዓለሙ መሪ ማዘጋጃ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ከ33 ሚሊዮን 455 ሺህ ብር በላይ በኾነ ወጭ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አጠናቅቋል ነው ያሉት መምሪያ ኅላፊው፡፡

በጠገዴ ወረዳ የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር 18 ሚሊዮን 954 ሺህ ብር በላይ በኾነ ወጭ የውስጥ ለውስጥ ጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ እና ከ2 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ ግንባታ ተጠናቋል ነው የተባለው፡፡ በሦስቱ ከተሞች ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነቡት የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለዞኑ ትልቅ የመልማት ጅማሮዎች መኾናቸው ተገልጿል፡፡

አቶ ዓለሙ “ከተሞቻችን የነጻነት ብቻ ሳይኾን በራስ አቅም የመልማትም ተምሳሌት ኾነዋል” ብለዋል፡፡ የዞኑ ሕዝብ ከበርካታ ዓመታት ግፍ እና ጭቆና በኋላ እውነተኛ ነጻነቱን እና ማንነቱን ማግኘቱ ኹነኛ ስኬቱ ነበር፡፡ ከነጻነት ማግስት የዞኑ ሕዝብ ከፌደራል መንግሥት ለጥያቄው ተገቢ ምላሽ እና በጀት አጥብቆ እንደሚጠብቅ ገልጸው ሕዝቡ እና የዞኑ አሥተዳደር በተናበበ መልኩ በራስ አቅም የመልማት ተምሳሌት መኾን እንደሚቻል አሳይተዋል ነው ያሉት መምሪያ ኅላፊው፡፡ በዞኑ ውስጥ 1 መካከለኛ ከተማ፣ 4 አነስተኛ ከተሞች፣ 5 መሪ ማዘጋጃ ቤት፣ 6 ንዑስ ማዘጋጃ ቤት እና 9 ታዳጊ ከተሞች እንደሚገኙ ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።
Next article“ነጻነት ተፈጥሯዊ መብት ነው፤ የተነጠቅነውም ያስመለስነውም ተፈጥሯዊ መብታችንን ነው” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ