
ባሕር ዳር: ሐምሌ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሐረር ከተማ ሐረር ከሰሃራ በታች ካሉ ከተሞች የመጀመሪያዋ የዓለም ቅርስ ከተሞች ድርጅት (Organization of World Heritage Cities) አባል ከተማ ኾና ተመዝግባለች።
\
የሐረሪ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪም ካናዳ ሀገር ኩቢክ ከተማ በተካሄደው የፊርማ ስነስርዓት ሐረር ከተማ የዓለም የቅርስ ከተሞች አባል ሆና የተመዘገበችበት ፊርማ አኑረዋል።
ሐረር ከተማ 115 ሀገራትን በአባልነት በያዘው የቅርስ ከተሞች ድርጅት ከፈረንጆች አቆጣጣር ከሰኔ ወር 2023 ጀምሮ ነው የተመዘገበችው።
ሐረር ከተማ የቅርስ ከተሞች መካከል አንዷ ኾና መመዝገቧ ከተማዋ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለማልማት እና ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
የቅርስ ከተሞች በጋራ ጉዳዮቻቸው ተመካክረው አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግዳሮቶችን ለመሻገርና እድሎችን ለማስፋት እንደሚጠቅም ይታመናል።
ሐረር ከተማ የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ዓለም አቀፍ ቅርሶች መገኛ ከተማ ከመኾኗ በተጨማሪ ከተማዋ ዜጎች በሰላም፣ በመቻቻልና በአብሮነት የሚኖሩባት ከተማ በሚል በተባበሩት መንግስት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ተቋም ዩኔስኮ እውቅና እንደተሰጣት ይታወሳል።
የሐረሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያመለክተው በፊርማ ስነ ስርአቱ ላይም የሀረሪ ክልል ርእስ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ ፣ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አሪፍ መሀመድን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማእከል ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሊድ አልዋን ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!