
ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ኃብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአስፈፃሚ ተቋማትን የሥራ አፈፃፀም ገምግሟል። የአስፈፃሚ ተቋማት ኀላፊዎችም ከቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) ትምህርት በባሕሪው ተከታይነት ያለው የረጅም ጊዜ ሥራ የሚጠይቅ መኾኑን ገልጸዋል። የመጽሐፍ እጥረትን ለመቅረፍ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መፃሕፍት መታተማቸውን ተናግረዋል። የመጽሐፍት ችግርን ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥት የወሰደው ተነሳሽነት ከፍተኛ መኾኑንም አስታውቀዋል። የታተሙ መጽሐፍትን ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ አሰራጭተው እንደሚጨርሱም ተናግረዋል። በጦርነቱ የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊው የመልሶ ማቋቋም ሥራው ከጉዳቱ አንፃር በቂ አለመኾኑንም ገልጸዋል። በቀጣይ የመልሶ ማቋቋም ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የነብስ ወከፍ በጀት በመመደብ የትምህርት ሥርዓቱን መደገፍ እንደሚገባም ተናግረዋል። የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ በትኩረት መሥራታቸውንም አስታውቀዋል። የባለፈው ዓመት በፈተናው ጊዜ በተማሪዎች የታየው ችግር እንዳይከሰት እስከ መጨረሻው ድረስ በትኩረት እንደሚሠሩም አመላክተዋል።
በብልሹ አሠራር የሚቸገር መምህር አይኖረንም ብለዋል። በትምህርት ቢሮው ያለው አገልግሎት አሰጣጥ እና የሥራ ባሕል ጥሩ መኾኑንም ገልጸዋል። ቢሮው ከዞኖች ጋር ያለው ትስስር ቀልጣፋና ጥብቅ መኾኑንም አንስተዋል። ችግሮቻችንን የምንሸፋፍንበት ምንም አይነት ምክንያት የለንም፣ ችግሮቻችንን በግልጽ እያወጣን መፍትሔ እንዲያገኙ እንሠራለን ነው ያሉት። በሦስት ዓመት ውስጥ የትምህርት ቤቶች ደረጃዎችን ለመቀየር እንሠራለንም ብለዋል። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ካልተቻለ የትምህርት ጥራትም አብሮ እንደሚወርድ ነው የተናገሩት።
የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው መምህራን እና ተማሪዎች እንዳሉም ገልጸዋል። የትምህርት ጥራት ችግር መኖሩንም አንስተዋል። የትምህርት ጥራት ችግር እንዲፈታ ተገቢውን እገዛና ክትትል እናደርጋለንም ነው ያሉት። የመሪዎች፣ የመምህራን፣ የተማሪዎች እና የወላጆች ትስስር የጠበቀ እንዳልኾነም አንስተዋል። ትስስሩን ማጠናከር እና የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ይገባልም ነው ያሉት።
የጎልማሶችን ትምህርት በሚፈለገው ልክ ከፍ ለማድረግ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል። የግል ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ መመሪያ ማዘጋጀታቸውን የተናገሩት ኀላፊው ከመመሪያው የሚያልፍ ካለ እርምጃ እንወስዳለንም ብለዋል። ተፈናቃይ ሕፃናትን እየደገፉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ከቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሱ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን በመውሰድ እንደሚሠሩባቸውም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ መልካሙ አብቴ (ዶ.ር) የጤና ተቋማትን ተደራሽነት ለማስፋት እየሠራን ነው፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም ነው ያሉት። ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጄክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውንም አስረድተዋል። የአንቡላንስ ችግሮችን ለመፍታት ለጤና ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረባቸውንና ምላሹን እየጠበቁ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ሕፃናት ላይ መሥራት የመቀንጨር ችግርን ይቀርፋል ያሉት ዶክተር መልካሙ መቀንጨርን ለመቀነስ የሁሉንም ተቋማት ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት። ለባሕል የሕክምና ባለሙያዎች እውቅና በመስጠት ቁጥጥር እያደረጉ እያሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የወባ በሽታን ለመከላከል በትኩረት ይሠራልም ብለዋል። የጤና ኤክስቴንሽን ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ መኾኑን ያነሱት ዶክተር መልካሙ ችግሮች ግን ሙሉ ለሙሉ ተቀርፈዋል ማለት አይደለም ነው ያሉት። በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን በተቻለ መጠን የጤና አገልግሎት እየሠጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የተነሱ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን ወስደው እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!