
ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 100 ወረዳዎች በአፈር አሲዳማነት መጠቃታቸውን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል፡፡
የአፈር አሲዳማነት ችግር በክልሉ የምርት እድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የቢሮው ኀላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡
ኀላፊው እንዳሉት በአማራ ክልል 10 ዞኖች የሚገኙ 100 ወረዳዎች በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ ናቸው፡፡ በክልሉ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታሩ የአሲዳማነት ችግር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩ ከፍተኛ አሲዳማነት ያለበት ሲኾን ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ 6ዐዐ ሺህ በላይ ሄክታሩ በከፍተኛ አሲዳማነት ምክንያት ምንም ዓይነት ምርት እንደማይሰጥ አንስተዋል።
ምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ደግሞ ከፍተኛ የአሲዳማነት ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡
በክልሉ የሚታየውን የአፈር አሲዳማነት ችግር ለመቅረፍ ቢሮው እየሠራ መኾኑንም ኀላፊው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በደጀን ወረዳ የኖራ ድንጋይ ማምረቻ በማቋቋም በከፍተኛ የአፈር አሲዳማነት ተጋላጭ ለኾኑ አካባቢዎች የማቅረብ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ የማምረቻ ወፍጮው በቀን የማምረት አቅም ዝቅተኛ በመኾኑ ለሁሉም የችግሩ ተጋላጭ አካባቢዎች ማቅረብ አልተቻለም ብለዋል፡፡
ችግሩ ካለው ስፋት አኳያ በቅርቡ በመርሃ ቤቴ ወረዳ ላይ የኖራ ማምረቻ ወፍጮ ማቋቋም መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የኖራ ማምረቻ ወፍጮዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!