በጦርነት ምክንያት በደረሰባቸው ጉዳት ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ባለሀብቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

40

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰበትን በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ የሚገኘውን ኮረብቲት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለ አራት ክፍል አንድ ብሎክ የመማሪያ ክፍል ግንባታ ለማካሄድ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

የመማሪያ ክፍሉን ግንባታ ሩጋስ የኤሌክትሮኒክ እቃዎች አምራች ሙሉ ወጭውን በመሸፈን እንደሚያሠራው በሥነ-ሥርዓቱ ተገልጿል፡፡

የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አብዲ ይማም ኮረብቲት አንደኛ ደረጃ ትምህርት በጦርነቱ በደረሰበት ጉዳት ከደረጃ በታች የኾነ ትምህርት ቤት መኾኑን ገልጸዋል።

ሩጋስ የኤሌክትሮኒክ እቃዎች አምራች ለትምህርት ቤቱ ላደረገው ድጋፍ ምሥጋናቸውን ገልጸው ሌሎች ባለሀብቶችም ለትምህርቱ ዘርፍ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መምህር አብዲ ጠይቀዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አብዱ ሁሴን በዞኑ ከደረጃ በታች የኾኑና በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት ለመገንባት መንግሥት የሚያደርገው ጥረት በቂ ባለመኾኑ ባለሀብቶች እንዲሳተፉና የተማሩባቸውን ተቋማት እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የመሰረት ድንጋዩን ከማስቀመጥ በተጨማሪም በሚኒስቴር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ሥርዓት አስተባባሪ አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር የተመራ ልዑክ በተገኘበት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

ዘጋቢ:- ከድር አሊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፊታችን ሀምሌ 10/2015 ዓ.ም በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ በንቅናቄ መሳተፍ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አህመድ ሽዴ አሳሰቡ።
Next articleአሲዳማ አፈርን ለማከም እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡