የፊታችን ሀምሌ 10/2015 ዓ.ም በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ በንቅናቄ መሳተፍ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አህመድ ሽዴ አሳሰቡ።

102

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ግብርና ቢሮ እያከናወናቸው በሚገኙ ሥራዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። ኀላፊዎቹ በባሕርዳር ከተማ የሚገኘው የአሳ ዝርያ ማዕከል እና የአቮካድ ልማት ሥራዎችንም ተመልክተዋል።

በአማራ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው “በጂ.ፒ.ኤስ” የታገዘ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ወደ ሌሎች ክልሎችም መስፋት የሚገባው ተሞክሮ መኾኑን ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል። በ2015 ዓ.ም የክረምት ወራት ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተሠራ የሚገኘው ሥራ ቀድሞ መጀመሩ ለአረንጓዴ አሻራ ትኩረት መሠጠቱ ማሳያ እንደኾነ ነው ያነሱት። የፊታችን ሀምሌ 10/2015 ዓ.ም በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይም በንቅናቄ መሳተፍ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሩ በተለይም ደግም የስንዴ፣ በቆሎ፣ የሩዝና የአኩሪ አተር ምርታማነትን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የአርሶ አደሩን ፍላጎት አሁንም ማሟላት ባይቻልም የማዳበሪያ እጥረትን ለመፍታት የፌዴራል መንግሥት እስከ 21 ቢሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ እያስገባ መኾኑንም ጠቅሰዋል። የቀረበውን ግብዓትም በፍትሐዊነት እና በወቅቱ ተከታትሎ ማሰራጨት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጣና ሐይቅ አሳ እንዳይቀንስ እየተደረገ የሚገኘው የአሳ እርባታ ሥራ ተሞክሮን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባው ገልጸዋል።

ክልሉ ለግብርና ሥራ ካለው አቅም አኳያ በቀጣይ ትኩረት በመስጠት ውጤታማነቱን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአምስተኛዉ ግራንድ አፍሪካን ረን በአሜሪካ ዲሲ በመጪዉ ጥቅምት ሊካሄድ ነው።
Next articleበጦርነት ምክንያት በደረሰባቸው ጉዳት ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ባለሀብቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተጠየቀ።