አምስተኛዉ ግራንድ አፍሪካን ረን በአሜሪካ ዲሲ በመጪዉ ጥቅምት ሊካሄድ ነው።

44

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ ኢትዮጵያዊያን የኦሎምፒክ አትሌቶች እና የዓለም ሻምፒዮኖች በዚህ ዝግጅት ላይ በክብር እንግድነት ይሳተፋሉ። ባለፉት ዓመታት ፈጣን እድገት እያሳየ የመጣው ግራንድ አፍሪካን ረን በመጪዉ ጥቅምት 3/2016 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

በዝግጅቱ ላይ ከ20 በላይ ታዋቂ የኦሎምፒክ አትሌቶች እና የዓለም ሻምፒዮን የሀገር ባለውለታዎች ተሳታፊዎችን ለማበረታታት የሚካፈሉ ሲኾን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ በርካታ ስመ ጥር አትሌቶች የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች እና ዝነኛ ግለሰቦች በክብር እንግድነት እንደሚገኙበት ተገልፆል።

በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ዝግጅት፤ ኢትዮጵያዊያንን ማሰባሰብ፣ የመጀመሪያው ትውልድ ልጆችን ከባሕላቸው ጋር የበለጠ ማቀራረብ፣ እና ለተለያዩ በጎ ሥራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዓላማው አድርጎ የሚከናወን ነው። በዚህ ዝግጅት፥ በሺዎች የሚቆጠሩ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉም ታውቋል።

አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ከመጀመሪያው ውድድር ጀምሮ በአካል በመግኘት አዘጋጆቹን ስትደግፍ የቆየች መኾኗ የሚታወቅ ሲኾን፣ ለታየው እድገት አድናቆቷን ገልጻለች። ዝግጅቱ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ከሀገር ውጪ ያሉ ወገኖችን የሚያሰባሰቡበት መድረክ በመኾኑ ልዩ ትርጉም አለውም ብላለች።

የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ባለድሉ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ “ኢትዮጵያን በበጎ መልክ ለማሳወቅ ጉልህ ድርሻ ባለው መድረክ ላይ በመሳተፌ ደስተኛ ነኝ” ብሏል። ቀኑንም በአብሮነት በደማቅ ሁኔታ እንድናሳልፍ ጥሪ አቀርባለሁ ነው ያለው።
የግራንድ አፍሪካን ረን ዋና አዘጋጅ ጋሻው አብዛ (ዶ.ር) ዝግጅቱ ከአንድ ቀን የ5 ኪሎ ሜትር የቤተሰብ ሩጫነት የበለጠ ፋይዳ ያለው መርሃ ግብር መኾኑን ጠቁመዉ፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማቀራረብ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። አያይዘውም፣ ከሩጫው ጎን ለጎን፥ ለሚኖሩበት የአሜሪካ ማኅበረሰብና ለትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የጎላ አስተዋፅኦ ላደረጉ የዲያስፖራ ወገኖች ሽልማት የሚሰጥበት መድረክ እንደኾነም አብራርተዋል።

ባለፉት ሦስት ዝግጅቶች፣ የሀገሪቱ ብርቅዬ አትሌቶች ማለትም ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ የዲባባ ቤተሰብ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ስለሺ ስህን፣ ቁጥሬ ዱለቻ እና ሌሎችም በክብር እንግድነት ተገኝተዉበታል። ለዚህ የ5 ኪሎ ሜትር የቤተሰብ ሩጫ የወድድሩ ምዝገባ በአዘጋጆቹ ዌብሳይት በኦንላይን www.africanrun.com ላይ ከሐምሌ 15/2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- ግርማ ሞገስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፋሲለደስ ስታዲየም ዕድሳት ሊደረግለት ነው” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር
Next articleየፊታችን ሀምሌ 10/2015 ዓ.ም በሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ በንቅናቄ መሳተፍ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አህመድ ሽዴ አሳሰቡ።