
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 06/2012ዓ.ም (አብመድ) በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአብክመ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) ምክክሩ ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው ብለዋል። የምክር ጉባኤው ለአንድ ዓላማ የቆሙ አካላት ወደ አሰቡበት ግብ ለመድረስ ትልቅ ሚና እንዳለውም ተናረዋል፡፡ በምክክሩ አሠሪዎች እና ሠራተኞች ያጋጠሟቸውን ችግሮችና፣ የቀሰሟቸውን መልካም ተሞክሮዎችና ወደ ፊት ሊወሰዱ የሚገባቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎች የሚመክሩበት እና ስለሠራተኛና አሠሪ ሕግና ፖሊሲዎች ግንዛቤ የሚጨብጡበት እንደሆነም አመላክተዋል።
‹‹በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ ጥሩ የሚባል የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ አለ›› ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ይህን ውጤታማ ለማድረግ የአሠሪና ሠራተኛን ግንኙነት መልካም ማድረግና የሠራተኞችን ጤንንት መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ውይይቱም በሠራተኛ እና አሠሪ ዙሪያ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶች በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሏል። በአሠሪዎች በኩል የሠራተኞች መደራጀት የማያስደስታቸው እና በሶሻሊዝም ጊዜ የነበረውን የላብ አደሩን የበላይነት አስተሳሰብ የሚሠጉ ቁጥራቸው ቀላል አለመሆኑን ኃላፊዋ ገልፀዋል። በሠራተኛውም በኩል ለራስ ጥቅም እንጂ ለድርጅቱ ዕድገትና ትርፋማነት እንዲሁም የሠራተኛ ግዴታ ላይ ትኩረት አለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡
በመንግሥትም በኩል ሠላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት እንዲኖር፣ ምቹ የሥራ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፣ የሠራተኞች ደኅንነት እንዲጠበቅ በማድረግ በኩል ክፍተት መኖሩ ነው የተገለጸው። የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መዋቅራዊ አደረጃጀቱም በ13 ወረዳዎች ብቻ ያለና በዞኖች ተንጠልጥሎ የቀረ እንደሆነም በውይይቱ ተነስቷል።
ማኅበረሰቡ ከቢሮው ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት በሚፈለገው ልክ እያገኘ እንዳልሆነም ዶክተር ሙሉነሽ ተናግረዋል። እንደ ሀገርም ትኩረቱ አናሳ እንደሆነ የገለፁት ቢሮ ኃላፊዋ ከምክክር ጉባኤው ጠቃሚ ግብዓቶችን በመውሰድ ክፍተቶችን በመቅረፍ ለሀገሪቱ ብልፅግና መሥራት እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።
በጉባኤው የተገኙት የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና የዓለም የሥራ ድርጅትም በጋራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
በጉባኤው በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ፣ የዓለም ሥራ ድርጅት የኢትዮጵያና አካባቢ ዳይሬክተር ተወካይ፣ አጋር አካላት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። ጉባኤው ለሁለት ተከታታይ ቀናት ይቆያል።
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ