“የፋሲለደስ ስታዲየም ዕድሳት ሊደረግለት ነው” የጎንደር ከተማ አሥተዳደር

42

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፋሲል ከነማ በ2013 ዓ.ም በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን ከኾነ በኃላ በፋሲለደስ ስታዲየም ጨዋታዎችን ማከናወን አልቻለም።

ዐፄዎቹ በሜዳቸው ጨዋታ ላለማስተናገዳቸው ምክንያት ደግሞ ፋሲለደስ ስታዲየም የሊግ ካምፓኒውን ዝቅተኛ የመጫወቻ መስፈርት አሟልቶ ባለመገኘቱ ነው። ችግሩን ለመፍታት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ስታዲየሙን ለማደስ እንቅስቃሴዎች መጀመሩን ገልጧል።

በጉዳዩ መግለጫ የሰጡት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ የስታዲየሙ ዕድሳት ሐምሌ/2015 ዓ.ም አጋማሽ ተጀምሮ በሁለት ወራት ውስጥ ሥራው ይጠናቀቃል ብለዋል። ለፋሲለደስ ስታዲየም ዕድሳት በሀገር ውስጥ ኾነ በውጭ የሚኖሩ የክለቡ ደጋፊዎች እገዛ እንዲያደርጉ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል። የስታዲየሙ ዕድሳትም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሠራ እንጅ ከመንግሥት በጀት የማይጠቀም መኾኑን አቶ ባዩህ አብራርተዋል።
የፋሲለደስ ስታዲየምን በተቀመጠው ጊዜ በማጠናቀቅና የሊግ ካምፓኒውን ዝቅተኛ መስፈርት በማሟላት ፋሲል ከነማ በ2016 የውድድር ዘመን በሜዳው ጨዋታዎችን እንደሚያከናውንም አቶ ባዩህ ጠቁመዋል።

የስታዲየሙ ዕድሳት በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ጎንደር እንዲጫወቱ ዕድል ይፈጥራል፤ ይህም ለቱሪዝሙ መነቃቃት ፋይዳው የጎላ ነው ያሉት አቶ ባዩህ የስታዲየሙን ዕድሳት ለማፋጠን ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ ስለመኾኑም አስረድተዋል።

የኮሚቴው አባል አቶ ሳሙኤል አማረ እና ትዕግስት ሲሳይ ኅብረተሰቡ በተለያየ መልኩ ድጋፍ የሚያደርግበትን ኹኔታዎች እያመቻቸን ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽምጠ ዊከ ጋዜጠ ሲን 15/2015 ዓ.ስ
Next articleአምስተኛዉ ግራንድ አፍሪካን ረን በአሜሪካ ዲሲ በመጪዉ ጥቅምት ሊካሄድ ነው።