የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ በፎርብስ መጽሔት ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ውስጥ ተካተቱ::

246

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 06/2012ዓ.ም (አብመድ) ፎርብስ በዓመታዊ መቶ ታላቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴን አካትቷል፡፡ በአውሮፓውያኑ 2018 ጥቅምት ወር በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውንም መጽሔቱ ጠቅሷል፡፡ በአፍሪካ በርዕሰ ብሔርነት መንበረ ስልጣን ላይ ያሉ ብቸኛ ሴት ናቸው፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሰሙት የመጀመሪያ ንግግራቸው ለሴቶች ድምፅ ለመሆን ቃል ገብተዋል፤ ስለአንድነት አስፈላጊነትም አፅዕኖት መስጠታቸውን ጽሑፉ አስታውሷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የመንግሥት ቁጥጥርን ማላላት ላይ አተኩረው ከወሰዷቸው የለውጥ እርምጃዎች አንድ አካል ሆኖ የፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ ሹመት ተመላቷል፤ ለወግ አጥባቂዋ ሀገር ኢትዮጵያ የፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ መሾም መልካም አርዓያ የሚሆን እንቅስቃሴ መሆኑን ጽሑፉ አትቷል፤ ለፆታ እኩልነት በር የከፈተ መሆኑን በማስገንዘብ፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ለጾታ እኩልነት ከጥንትም ትኩረት መስጠቷን ታሪኳ ያመላክታል፡፡ ከንግሥተ ሳባ ጀምሮ በተለያዩ ዘመናት ሴቶች ሀገር መርተዋል፤ በዘመናዊት ኢትዮጵያም እቴጌ ጣይቱና እቴጌ ዘውዲቱ ተጠቃሽ በከፍተኛ የኃላፊነት እርከን ሀገር የመሩ ሴቶች ናቸው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የበርካታ ሥራ ልምድ ባለቤትና ከፍተኛ ዲፕሎማትነት ሆነው ያገለገሉት ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ በዚህ ወቅት በዓለም ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሴቶች መካከል 93ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን ፎርብስ ይፋ አድርጓል፡፡
በኪሩቤል ተሾመ

Previous articleበአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በጓጉሳ ሽጉዳድ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ13 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡
Next articleየአብክመ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የመንግሥት፣ የአሠሪና ሠራተኛ የሦስትዮሽ ምክክር ጉባኤ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።