
ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለተያዘው እቅድ 361 ሺህ 415 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ፤ በአንድ ጀንበር ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 9 ሺህ 500 የመትከያ አካባቢዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።
ለ500 ሚሊዮን ችግኞች መትከያ 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ሚኒስትር ዴታው ተናግረዋል።
በዕለቱ በየአካባቢው የሚደረጉ የችግኝ ተከላዎችን ከስፍራው በቀጥታ ለዓለም ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ የካርታና GREENLEGACY.ET የዌብ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር 9 ሺህ 500 ቦታዎችን በካርታ የማካተትና ድረገፅ በማበልፀግ ወደ ሥራ መገባቱን ፕሮፌሰር እያሱ ተናግረዋል።
በእለቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሁሉም ቦታዎች በተመደቡ ባለሙያዎች ወደ ማዕከል ሁነቱ የሚደርስ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለተያዘው እቅድ ዜጎች ሁሉ በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንዲያኖሩ ሚኒስትር ዴታው ጥሪ አቅርበዋል።
በእለቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በችግኝ ተከላው እንደሚሳተፍ ጠቅሰው እቅዱ የሚሳካ መሆኑንም የጸና እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 60 በመቶው ለጥምር ደን ግብርና፣ 35 በመቶው ለተፋሰስ ልማትና ለደንሽፋን እንዲሁም አምስት በመቶው ለከተማ ውበት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ችግኞችን ወደ መትከያ ቦታ በጥንቃቄ በማድረስ፣ ማስቀመጫ ፕላስቲኮችን በጥንቃቄ በማስወገድ ኢንዲተክሉና ለተያዘው ግብ እርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በጥንቃቄና በሙያዊ መንገድ ችግኞች እንዲተከሉ የሚያግዙ ባለሙያዎችም በሁሉም አካባቢዎች የሚሰማሩ መሆኑም ተጠቅሷል።
አኢዜአ እንደዘገበው ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተደረገው ጥሪ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ትግበራ በተግባር የሚታይበት ይሆናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!