“የመከላከያ ሰራዊታችን የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ከምንጊዜውም በላይ በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

64

ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “የመከላከያ ሰራዊታችን የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ከምንግዜውም በላይ በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል” ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህን ያሉት “ምንጊዜም ለመዘመንና ለድል አድራጊነት እንዘጋጅ” በሚል መሪ ሃሳብ የዳሎል ማዕከላዊ እዝ ዓመታዊ ክብረ በዓል በጅማ ከተማ በተከበረበት ውቅት ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በመልዕክታቸውም የዳሎል ማዕከላዊ እዝ በእሳት የተፈተነና ለአገር ሉዓላዊነት አኩሪ ጀግንነት የከፈለ እዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የእዙ አባላት በቀጣይም በላቀ የግዳጅ አፈጻጸም ግዳጃቸውን ለመፈጸም ዝግጁነታቸውን ይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊቱ በዘመናዊ ትጥቅ በመደራጀት የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ከምንግዜውም በላይ በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የሰራዊቱ ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ተልዕኮውንም በብቃት ይወጣል ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ የጀግንነት ማዕከል የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በሀሰት በማጠልሸት የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል፡፡

የእነዚህ አካላት ዋነሻ ዓላማም ከባዕዳን ተልዕኮ በመቀበል ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊቱ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ባከናወናቸው ተግባራት በተለያዩ ክልሎች በሀሰተኛ መረጃዎች ተደናግረው በሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ አካላትን ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የመከላከያ ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ህልውና እና ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የትኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአስፈፃሚ አካላት ጠንካራ ሥራዎችን የበለጠ በማጠናከር ደካማ ጎኖቻቸውን እየፈቱ እንዲሄዱ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።
Next article“በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት ዝግጁ ሆኗል” የግብርና ሚኒስቴር