
ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ኃብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአስፈፃሚ ተቋማትን የሥራ አፈፃፀም እየገመገመ ነው። ቋሚ ኮሚቴው የተቋማቱን የመስክ ምልከታ በማድረግ፣ ከሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመያዝና የተቋማቱን ሪፖርት በማየት እንደሚከታተል አንስቷል። አስፈፃሚ ተቋማት ጠንካራ ሥራዎችን የበለጠ በማጠናከር ደካማ ጎኖቻቸውን እየፈቱ እንዲሄዱ አሳስበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ የቋሚ ኮሜቴውን ዓመታዊ ግምገማ አቅርበዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ለተቋማቱ አስተያየታቸውን እና ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።
ትምህርት ቢሮ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ ታይቶ የነበረው ችግር እንዳይደገም በቁጭት እየሠራ መኾኑ የሚበረታታ መኾኑ ነው የተመላከተው። ትምህርት ቢሮ የሚያስመሰግኑ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን አንስተዋል። የትምህርት ጥራት ችግርን ለመቅረፍ እየሠራው ያለው ሥራ አበረታች መኾኑም ተመላክቷል። ትምህርት ቢሮው አሁንም ማስተካከል የሚገባው ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተዋል። የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ችግር እንዳይገጥማቸው ትምህርት ቢሮው ምን እየሠራ እንደኾነ ተጠይቋል። ባለፈው ዓመት አፈታተኑ አዲስ በመኾኑ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ጫና ስለደረሰባቸው የተፈለገውን ውጤት ማሳካት አልቻሉም ነው ያሉት። ተማሪዎችን ወደ አልተገባ ሁኔታ የሚወስዱ አካሄዶችን ማስተካከል እንደሚገባውም አንስተዋል። አንዳንድ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አቅማቸው እየደከመ እና ለመማር ማስተማር ምቹነታቸው እየቀነሰ መጥቷል፣ ዘመኑን የዋጀ ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል።
የተማሪ ማቋረጥ ምጣኔ አሁንም አሳሳቢ በመኾኑ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ነው ያሉት። ከከተማ ራቅ ያሉ ቦታዎች ላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች ላይ ያለው ቁጥጥር እና ክትትል አናሳ መኾኑንም አንስተዋል። የግብዓት አቅርቦት ችግር መኖር፣ የቀረበውን ግብዓትም በአግባቡ የመጠቀም ችግር መኖሩንም አመላክተዋል። የጎልማሳ ትምህርት አሰጣጥ በክልሉ የለም በሚባልበት ደረጃ መድረሱንም ገልጸዋል። የፕላዝማ ትምህርት ሥርዓትም መቀነሱን አንስተዋል። የግል ትምህርት ተቋማት ላይ የሚነሱ ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት። የተማሪ ምገባን በክልሉ በሚፈለገው ልክ ማስቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል። ምገባ እየተካሄደባቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየተከታተሉ መኾናቸውንም አንስተዋል።
በኅብረተሰብ ተሳትፎ የሚሠሩ ትምህርት ቤቶችን ልምድ ማሳደግ መልካም መኾኑም ተገልጿል። በዓመቱ ሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ ቢታቀድም በተባለው ልክ መኾን አልቻለም ነው የተባለው።
ከጤና ቢሮ አንፃር የሚሰጡ አስተያየቶችን እየወሰዱ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት አበረታች መኾኑን አንስተዋል። የደም ባንክ ላይ እየተሠራው ያለው ሥራ መልካም መኾኑ ተነስቷል። የኦን ላይን የጤና መረጃ ሥርዓት መዘርጋቱ አበረታች መኾኑንም አንስተዋል። የጤና መድኅን ሥርዓቱም መልካም ነው ተብሏል። በጤናው ዘርፍ አሁንም ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን ነው ያነሱት። የወባ በሽታን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ሥራ አነስተኛ ነው ብለዋል። በተለይም የወባ ስርጭት በሚበረክትባቸው በረሃማ አካባቢዎች ላይ በትኩረት መሠራት አለበት ነው ያሉት። የወባ በሽታ የሚስፋፋበትን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ነው የተመላከተው። ከእናቶች ወሊድ ጋር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን መፍታት ይገባልም ብለዋል።
የጤና ተቋማት ላይ የተጀመሩ ፕሮጄክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል። የመድኃኒት እና የግብዓት አቅርቦት ችግሮች መኖራቸውንም አንስተዋል። በሆስፒታሎች እና በጤና ጣቢያዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዳሉም ተመላክቷል። የጉልበት ሠራተኞች በሚበዙባቸው የበረሃማ አካባቢዎች የጤና ተቋማትን ማስፋፋት እና የጤና አገልግሎቱን ማሻሻል ይገባልም ብለዋል።
በባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ የተሠራው ሥራ መልካም መኾኑን አንስተዋል። ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ሁነቶችን በስፋት ለማስተዋወቅ የተሰጣቸው ትኩረት መልካም ነው ብለዋል። ለቋሚ ቅርሶች የይዞታ ማረጋገጫ በመስጠት በኩል ክፍተት መኖሩንም አመላክተዋል። ቅርሶች ምዝበራ እየደረሰባቸው ናቸው፣ የቅርሶችን ምዝበራ ለመከላከል እንዲሠራም ጠይቀዋል።
የተመዘገቡ እና ያልተመዘገቡ በርካታ ጥንታዊ ቅርሶች አሉ፣ ቅርሶችን በአግባቡ መያዝ፣ ለትውልድ ማሳየት፣ የገቢ ምንጭ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስፋትና ማስተዋወቅ ላይ ያለውን ክፍተት መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ኮሚሽን የሰው ኃይልን በአግባቡ በመመደብ በኩል የሚስተዋለውን ችግር መፍታት አለበት ብለዋል። ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል። ተገልጋዮችን በአግባቡ ያለማስተናገድ ችግር እንዲፈታም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!