
ባሕር ዳር: ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አሕመድ ሽዴን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተሠሩ ሥራዎችን ተመልክተዋል።
ቢሮው በአረንጓዴ አሻራ ልማት እስከ አሁን ያለውን አፈጻጸምና ያለው ቅድመ ዝግጅት፣ የመኸር እርሻ ዝግጅት፣ የልማት ትሩፋት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተሠሩ ሥራዎችን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) ለፌዴራል የሥራ ኀላፊዎች አቅርበዋል።
ቢሮ ኀላፊው እንዳሉት በ2015 ዓ.ም የክረምት ወራት በአማራ ክልል 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 25 በመቶ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በመኖ ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል ።
ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም 260 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም አብራርተዋል። እስከ አሁንም 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ጉድጓድ ተዘጋጅቷል።
ባለፉት አራት ዓመታት ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ የተተከለ ሲኾን 80 በመቶ የጽድቀት መጠን እንዳለውም ገልጸዋል።
ዘጋቢ።- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!