
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአስፈጻሚ ተቋማትን የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቺአምላክ ገብረ ማርያም የተቋማቸውን አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም በየደረጃው ያሉ ተቋማትን በተገቢው እንዲፈጽሙ የማድረግ እና በማይፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ የመውሰድ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ለተቋማት ድጋፍና ክትትል የማድረግ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሕዝብ የሚያነሳቸውን የአግልግሎት አሠጣጥ ችግር ለመቅረፍ ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሯ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ አሁንም ችግር መኖሩንም ገልጸዋል። የተቋማት መሪዎችን ጨምሮ በቢሮ ተገኝቶ ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት የማይሰጡ ተቋማት መኖራቸውንም አንስተዋል። አገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽ፣ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ችግሮቹ ግን አሁንም ሰፊ መኾናቸውን ነው ያነሱት።
በተወሰኑ ተቋማት ላይ የሥራ ሰዓትን የማያከብሩ ሠራተኞች መኖራቸውንም ገልጸዋል። መሪዎችም ቀን መድቦ ተገልጋዮችን ከማስተናገድ ይልቅ በደራሽ ሥራ እንደሚጠመዱም አንስተዋል። ተቋማት የዜጎችን ቻርተር በማዘጋጀት በኩልም ክፍተት እንዳለባቸው ነው ያመላከቱት።
በተደጋጋሚ የሚነሳውን ከሠራተኞች ለሚቀርበው የትምህርት ዝግጅት እና የሥራ ልምድ ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል። በጦርነቱ ምክንያት መረጃቸው የጠፋባቸው ሠራተኞችን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሠራታቸውንም ገልጸዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች የሁለት ዓመት እርከን አለመፈቀድ፣ ለዝቅተኛ የመንግሥት ሠራተኞች ወቅቱን ያገናዘበ ድጎማ አለመደረግ ችግሮች እንደኾኑባቸውም አንስተዋል። የሥራ ሥነ ምግባር እና አገልግሎት አሰጣጥ፣ የለውጥ እና ለውጥ አመራር ፣ ችግር ፈቺ የውሳኔ አሠጣጥ ፣ የስሜት ብልህነት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሥልጠና መስጠታቸውንም ገልጸዋል። የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።
የሕዝብን ጥያቄ የሚመልስና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያለው መሪ እንዲፈጠር የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት። ኮሚሽኑ በዓመቱ የደረጃ ምዘና ሰጥቷል ነው ያሉት። በጊዜያዊ አሥተዳደር ሥር የነበሩ አካባቢዎች በሙሉ መዋቅር መሥራት መቻሉን ያነሱት ኮሚሽነሯ ይሄም በክልሉ መንግሥት ያለውን አመኔታ እንዲጨምር አድርጓል ነው ያሉት።
የሰው ሃብት ልማት ላይ የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራር ለመቅረፍ በትኩረት መሥራታቸውንም አስታውቀዋል። አሁንም ከሕዝቡ የሚመጡ ብልሹ አሠራሮች መኖራቸውንም አመላክተዋል።
ፈቃድ ሳይሰጣቸው ቅጥር የሚፈጸሙ አሠራሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረጉ መኾናቸውን ያነሱት ኮሚሽነሯ አሁንም ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል። የሐሰተኛ ማስረጃ ይዘው የተቀጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች ላይ በተሠራው የማጣራት ሥራ ሐሰተኛ ማስረጃ ይዘው በተገኙ ሠራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት። ሠራተኞች ብቻ ሳይኾን ተቋማትም ተጠያቂ መኾናቸውም ተገልጿል፡፡ የሥነ ምግባር ችግር ባለባቸው ሠራተኞች ላይም እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።
አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ሲነሳ የነበረውን ደካማ አሠራርን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት። መረጃን ወረቀት አልባ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል። ኮሚሽኑ በተሰጠው ሥልጣን ልክ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በተቋማት ላይ የለውጥ አተገባበር ላይ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል አድጓል ብለዋል።
የሠራተኛው የኑሮ ውድነት ጫና፣ የተቋማት አግባብነት የሌለውና በጥናት ያልተደገፈ የሥራ መደብ ይፈቀድልኝ፣ የመደብ ይሻሻልኝ እና ሌሎች ችግሮች እንዳሉባቸው ነው የተናገሩት። በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የበጀት ችግር፣ ፋይል የወደመባቸው ሠራተኞች ጥያቄ ምላሽ አለማግኘት ችግር እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
በቀጣይ የአገልግሎት አሠጣጥን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የማድረግ፤ የሠራተኞችን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የሚያስችሉ አማራጮችን በማጥናት ሥራ እንሠራለንም ብለዋል። የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥም ለማሻሻል ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!