ንጋት ኮርፖሬት ካፒታሉ 16 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ ገለጸ፡፡

77

ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀትና ፋይናስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

ቋሚ ኮሚቴው በጠዋት መርሐ ግብሩ የሚከታተላቸውን የልማት ድርጅቶች የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ተከታትሏል።

የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና ንጋት ኮርፖሬት የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸማቸውን ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርቱ ንጋት ኮርፖሬት ከነበረበት ችግር ወጥቶ ወደ ተሻለ ትርፋማነት ተሻግሯል ያሉት የኮርፖሬቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምላኩ አስረስ (ዶ.ር) ናቸው። 30 የሚደርሱ ድርጅቶች ባለቤት የኾነው ንጋት ኮርፖሬት ካፒታሉ 16 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰም አስረድተዋል።

በተለይም ባለፉት 5 ወራት በንጋት ኮርፖሬት ሥር ያሉ አምራች ድርጅቶቹ አትራፊ መኾናቸውን ነው በሪፖርቱ ያመላከቱት። በዚህም 634 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት ታቅዶ 564 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ይህም የእቅዱን 88 ነጥብ 9 በመቶ ይሸፍናል ተብሏል፡፡ በክልሉ እያጋጠመ ያለውን የገበያ ጉድለት ለመሙላት 158 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሸቀጥ ንጋት ኮርፖሬት ለገበያ አቅርቧል ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡
ወደ ውጭ የሚላኩ የሀገር ውስጥ ሰብሎች ዋጋ መናር፣ በዓለማቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ አለመኾን እና የምንዛሬ ችግር ማጋጠሙንም ጨምረው አንስተዋል፡፡

ለቋሚ ኮሚቴው የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸሙን ያቀረበው የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በበኩሉ በሰው ኀይል፣ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂና በግንባታ ማሽነሪዎች በተሻለ መልኩ መደራጀቱ ተገልጿል።

በሰሜን ሽዋ በአዝማ ጫጫ፣ በደቡብ ጎንደር ማህለኛው ርብ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጣና በለስ ሜጋ ፕሮጀክቶች ወደ ተሻለ ሥራ እንዲገቡ የተሻለ ሥራ ተሠርቷል ተብሏል።

በደቡብ ወሎ ዞን በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የመጠጥ ውኃ ግንባታን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉንና አዳዲስ የውኃ ፕሮጀክቶችንም ወደ ሥራ በማስገባት ረገድ ጥሩ ሥራ ተሠርቷል ተብሏል።

የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግንባታ ግብዓቶችና የስሚንቶ አቅርቦት ለሥራው ተግዳሮት እንደኾነበትም ተነስቷል።

ቋሚ ኮሚቴው የሚከታተላቸውን ተቋማት ሪፖርት መከታተሉን ከሰዓትም የሚቀጥል ይኾናል።

ዘጋቢ:- ቻይና አየልኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምርት ዘመኑ በአማራ ክልል 8 ሚሊዮን ኩንታል የሩዝ ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን ግብርና ቢሮ ገለጸ።
Next articleአቶ አህመድ ሽዴ በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ “የሌማት ቱሩፋት” ሥራዎችን ጎበኙ።