በምርት ዘመኑ በአማራ ክልል 8 ሚሊዮን ኩንታል የሩዝ ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑን ግብርና ቢሮ ገለጸ።

88

ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2015/2016 ምርት ዘመን የሩዝ ኩታ ገጠም ዘር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምከም ወረዳ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) በምርት ዘመኑ 150 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ በመሸፈን 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው ብለዋል። ይህንን ለማሳካትም የክልሉ ግብርና ቢሮ ከታታሪ የክልሉ አርሶ አደሮች ጎን በመኾን በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። አማራ ክልል የሩዝ ምርት በሀገር አቀፍ ደረጃ 60 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝም ቢሮ ኀላፊው አመላክተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ዶ.ር) የሊቦከምከም ወረዳ ለሩዝ ምርት የሰጠው ትኩረት በክልሉ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት የሚኾን ነው ብለዋል።

ያለንን ጸጋ በመጠቀም ድህነትን ለማሸነፍ በምናደርገው ጥረት ሁሉ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁመን በማለፍ ውጤት ማስመዝገብ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም ከአፈር ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ የገጠመውን ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ዶክተር ኤርጎጌ ከአፈር ማዳበሪያ ጥገኝነት ለመውጣት መጣር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሮች በሀገራችን የማይመረተውን ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ለመተካት የተፈጥሮ ማዳበሪያን ጠንክረው እንዲያዘጋጁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልል ክለቦች ሻምፒዮናው ግማሽ ፍጻሜ ላይ ደርሷል!!
Next articleንጋት ኮርፖሬት ካፒታሉ 16 ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ ገለጸ፡፡