
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለ50 ሺህ ወገኖች የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና መደረጉንም የጤና ቢሮው አስታውቋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአስፈጻሚ ተቋማትን የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮን አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ዶክተር መልካሙ አብቴ በጤናው ዘርፍ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። በክልሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የኤች አይቪ ምክርና ምርምራ ተሰጥቷል ነው ያሉት። በክልሉ የኤች አይቪ ኤዲስ ምጣኔ 0 ነጥብ 6 በመቶ መኾኑንም ገልጸዋል። የቲቢ ልየታ ላይ ሠፊ ሥራዎችን መሥራታቸውንም ገልጸዋል። የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራም ተሠርቷል ብለዋል። 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የወባ ምርምራ ተሠርቶላቸው 666 ሺህ 352 ወገኖች ወባ ተገኝቶባቸዋል ተብሏል።
በክልሉ ውጤታማ የጤና ኤክስቴንሽን ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። በክልሉ 71 በመቶ የእማውራዎችና አባውራዎች የመጸዳጃ ቤት ሽፋን እንዳላቸውም ተመላክቷል። መጸዳጃ ቤት መቆፈር ብቻ ሳይኾን በተደረገው ጥናት 95 በመቶ እየተጠቀሙበት መኾኑ ተረጋግጧል ነው የተባለው።
ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ ቦታችን በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሥራዎች መሠራቱንም አስታውቀዋል። የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና ያለውን ክምችት ለመቀነስ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። በዓመቱ ለ50 ሺህ ለሚኾኑ ወገኖች የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል። በዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና የተሠራው ሥራ ታላቅ ክንውን መኾኑንም ገልጸዋል።
የሕክምና አግልግሎቱን ለማሻሻል በተሠራው ሥራ የሆስፒታሎች ትራንስፎርሜሽን 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 63 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል። 67 በመቶ ጤና ተቋማትን ፅዱና ምቹ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል። የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ከፍተኛ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። የቀዶ ሕክምና አገልግሎት አሠጣጡም ከፍ ማለቱን ነው የተናገሩት። የጤና ጣቢያ አግልግሎት አሠጣጥ ማሻሻያ ተሠርቷልም ተብሏል።
ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን ከመቆጣጠር እና ከመከላከል አንፃር ጥሩ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ኃላፊው ዜጎች የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ለፅኑ እና ለድንገተኛ አደጋዎች ሕሙማን የሚያገለግሉ የኦክስጂን ማምረታቻ ሥራዎችም ተሠርተዋል ነው ያሉት። በክልሉ ተፈናቅለው የሚገኙ ወገኖችን የጤና ችግር እንዳይገጥማቸው እየሠሩ መኾናቸውን እና በቀጣይም በትኩረት እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት።
በዓመቱ ለጤና ባለሙያዎች አዲስ የሙያ ምዝገባና ልየታ ተሠርቶላቸዋል ተብሏል። በክልሉ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የመድኃኒት ግዢና ስርጭት ተካሂዷልም ተብሏል። በአማራ ክልል በ184 ወረዳዎች የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥርጭት ትግባራ ተደርጓልም ነው ያሉት። በክልሉ 17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎችን የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል።
ከማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኀን 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧልም ነው የተባለው። የጤና መሠረተ ልማትን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ዶክተር መልካሙ 85 መካከለኛ እና ከፍተኛ ፕሮጄክቶችን ማጠናቃቀቸውንም ገልጸዋል። 382 ዝቅተኛ ፕሮጄክቶችን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
የጤና መዋቅር አለመሻሻል፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በሚፈለገው ልክ አለማደግ፣ የተቋማት የበጀት መጠን አለመመጣጠን፣ ቀልጣፋና በቂ የግብዓት አቅርቦት አለመኖር፣ ለቁጥጥር ሥርዓቱ በየደረጃው ያለው ቅንጅታዊ አሠራር አናሳ መኾን፣ በቂ የኾኑ የሕክምና መሣሪያዎች እና የላቦራቶሪ ሪኤጀንቶች አቅርቦት አለመኖር ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ከግንባታ ጋር በተያያዘ የግንባታ ጥሬ እቃ ዋጋ መጋነን፣ የዋጋ ማሻሻያ ካልተደረገ ወደ ግንባታ አንገባም በሚል ተቋራጮች ሥራ ማቆም እና ሌሎች ችግሮች እንዳሉባቸውም አስታውቀዋል።
በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋልም ብለዋል። በድንገተኛ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ተጠባባቂ በጀት መመደብ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የጤና ተቋማትን ተደራሽነት ለማስፋፋት መሠረተ ልማት እንዲሟላ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!