
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአስፈጻሚ ተቋማትን የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) የትምህርት ቢሮውን አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል። በሪፖርታቸውም የነፍስ ወከፍ በጀትን ማሻሻል ካልተቻለ የትምህርት ሥርዓቱን ይጎደዋል ብለዋል።
ዶክተር ማተብ በክልሉ ያሉ ኮሌጆች በተቻለ መጠን የደረጃ ማሻሻያ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ወቅቱን እና ጥራቱን የጠበቀ እቅድ በመያዝ ለተፈጻሚነቱ መሥራታቸውንም ተናግረዋል። ሥራዎቻቸውን በተደራጀ አግባብ እንደሚሠሩ የተናገሩት ኀላፊው የመልካም አሥተዳደር ችግርን ለመፍታት ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል። ቢሮው በጀቱን በአግባቡ መጠቀም መቻሉንም ገልጸዋል። ሥራዎቻቸውን ከወረቀት ንክኪ ለማራቅ በተሠራው ሥራ አበረታች ለውጥ መታየቱንም ተናግረዋል። የተማሪ ወላጆችን ማኅበር የማጠናከር ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመት የማኅበረሰብ ተሳትፎ ሥራ መሠራቱንም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። ተሳትፎው በገንዘብ ፣ በጉልበት እና በቁሳቁስ መኾኑንም አንስተዋል። ከደረጃ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶችን ታሪክ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤቶችን መገንባት በክልሉ በትኩረት ሊሠራበት የሚገባው ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል። እየተገነቡ ያሉ ትምህርት ቤቶች ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸውንም አስገንዝበዋል።
በትምህርት ቤቶች የንፁህ መጠጥ ውኃና የመፀዳጃ ቤት ማሟላት በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን ያነሱት ኀላፊው በቀጣይም በትኩረት ይሠራባቸዋል ነው ያሉት። በመልካም ሥነ ምግባር የታነፁና ለሥራ ዝግጁ የኾኑ ተማሪዎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የመምህራንን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በቁልፍ ተግባር ይዘው መሥራታቸውንም አስታውቀዋል።
በዓመቱ 210 ሺህ ተማሪዎችን በምገባ መርሐ ግብር ማካተት መቻሉንም ተናግረዋል። ክልሉ ካለው ሥፋትና ከሚጠበቅበት አንፃር በቂ አለመኾኑንም አንስተዋል። የተማሪዎችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አመላክተዋል። የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን ለመመለስ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ትምህርት ሚኒስቴርም ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው እየተደረገ ያለው ድጋፍ ግን ከወደመው ቁጥር አንፃር በቂ አለመኾኑን ነው ያነሱት።
ከደረጃ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶች እያልን መኖር የለብንም፤ የሚከፈለውን ዋጋ ከፍለን ታሪኩን መቀየር አለብን፤ በጋራ ከሠራን እንቀይረዋለን፣ ለቀጣዩ ትውልድም የተሻለ ነገር ማስረከብ አለብን ነው ያሉት ዶክተር ማተብ። በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋምም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚሻም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!