
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 06/2012ዓ.ም (አብመድ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በጓጉሳ ሽጉዳድ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አማረ ፈረደ አስታወቁ፡፡ ኃላፊው እንደተናገሩት ዛሬ ረፋድ 3፡00 በወረዳው አዲስ ዓለም በምትባል የገጠር ከተማ አካባቢ ነው የትራፊክ አደጋው የደረሰው፡፡
ከጅጋ ወደ ባሕር ዳር ተሳፋሪ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ‹ሚኒባስ› ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ ከነበረ ከባድ የጭነት መኪና ጋር ተጋጭቶ የ13 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ከባድ እና ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም አሉ፡፡
የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት እየተሠራ እንደሆነም ዋና ኢንስፔክተር አማረ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸውን ወደ አቅራቢያ የጤና ተቋም የመላክ እና የሟቾችን አድራሻ የመለየት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል በተያዘው ዓመት እየደረሱ ያሉ የትራፊክ አደጋዎችና እያደረሱ ያለው የጉዳት መጠን በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን አብመድ በተደጋጋሚ ዘገባዎቹ አመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው
ፎቶ፡- የጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት