ዛሬ አዲሰ አበባ የሱዳንን ግጭት በድርድር ለመፍታት በኢጋድ የተወከሉ መሪዎች ይወያያሉ።

45

ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ አዲሰ አበባ የሱዳንን ግጭት በድርድር ለመፍታት በኢጋድ የተወከሉ መሪዎች ይወያያሉ።

በኢጋድ የተወከሉ ሀገራት መሪዎች በውይይቱ ለመሳተፍ አዲሰ አበባ ከትናንት ጀምሮ እየገቡ ነው።

የሱዳንን የርስ በርስ ግጭት ለመፍታት ተፋላሚ ኀይሎችን ለማደራደር በአዲስ አበባ ዛሬ በመሪዎች ደረጃ ውይይት ይካሄዳል።

የኬኒያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶም(ዶ/ር) በኢጋድ የአራትዮሽ “ኳርቴት” የሱዳን እና ቀጣናዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች የመሪዎች ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ሲገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቀደም ሲልም የጅቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሃመድ አሊ የሱፍና የሰብዓዊ ጉዳዮች እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ (ኦቻ) ዋና ፀኃፊ ማርቲን ግሪፍትስ አዲስ አበባ ሲገቡ ሚኒስትር ዴኤታዋ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ጅቡቲ ባካሄደው 14ኛ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ያሉበት የአራት ሀገራት “ኳርቴት” የተሰኘ ኮሚቴ በማዋቀር የሱዳንን ግጭት ለማስቆም ውክልና መስጠቱ የሚታወስ ነው።

የመፍትሔ አፈላላጊ የምክክር መድረኩም በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ግጭቱን እየመሩ የሚገኙ አካላትን የማደራደርና የሰብዓዊ ድጋፍ የማቀላጠፍ ስራ ትኩረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

በኢጋድ 14ኛው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አራቱ ሀገራት ያሉበት የሰላም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የሱዳን ጦር መሪ ጀኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንንና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ሌፍተናንት ጀነራል ሙሀመድ ሀምዳን ዳጋሎን (ሔሜቲ) በአስር ቀናት ውስጥ ለማነጋገር አቅጣጫ ማስቀመጡም ይታወሳል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ኢጋድ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተክትሎም ሱዳን ላጋጠማት ወቅታዊ ችግር መፍትሔ ለመስጠትና በቀጣናዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ የአባል ሀገራት የመሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ተገኝተው ይወያያሉ።

የኬኒያ ፕሬዝደንት ዶክተር ዊሊያም ሩቶን ተከትሎም የጅቡቲ ፕሬዝደንት እስማዔል ዑመር ጉሌህ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ማያርዲትን ጨምሮ የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር የተቀሰቀሰው የሱዳን ግጭት ተባብሶ በመቀጠሉ በግጭቱ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀለ ንብረትም እያወደመ መሆኑ ይታወቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ በሐምሌ 03/2015 ዓ.ም ዕትሟ
Next articleዶክተር አምባቸው መኮንን በደብረታቦር ከተማ ትምሕርት ቤት ተሰየመላቸው።