
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ አባላት የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የመንግሥት ሥራ አፈጻጸምን እና በቀጣይ የክረምት ወራት እቅድ ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ በግብርናው ዘርፍ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ቱሩፋት፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች እንደነበሩ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ክልሉ በጦርነት እና በጸጥታ ችግር ውስጥ የከረመ ቢኾንም የልማት እቅዶችን ዳር ለማድረስ በተደረገው የጋራ ርብርብ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ አክለውም ባለፈው የምርት ዘመን የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ በተደረገው አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። በቀጣይም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ አንስተዋል።
በቀጣይ የክረምት ወራት የሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የመኸር ሰብል ልማት፣ የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አገልግሎትና ሌሎች ወቅታዊ ሥራዎች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆኑ የክልሉ መንግሥት ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል አስተማማኝ ሰላም አስፈላጊ በመኾኑ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ መልክ ማስያዝ ይኖርብናል ብለዋል።
ከክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የሰላምና መረጋጋት ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ በመኾኑ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!